ቀጥታ፡

በክልሎቹ የከተራና የጥምቀት በዓላት በሰላም ተከብረው መጠናቀቃቸውን ፖሊስ አስታወቀ

ሚዛን አማን፣ ሀዋሳ፤ ጥር 11 ቀን 2015 (ኢዜአ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች፣ በደቡብና ሲዳማ ክልሎች የከተራና የጥምቀት በዓላት በሰላም ተከብረው መጠናቀቃቸውን የየክልሎቹ ፖሊስ ኮሚሽኖች አስታወቁ

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር ነብዩ ኢሳያስ እንደገለጹት ነገ ወደ መንበረ ክብራቸው ከሚመለሱ ታቦታት በስተቀር ሁሉም በሰላም ወደ አብያተ ክርስቲያናት ተመልሰዋል።

በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶች፣ በየደረጃው የሚገኙት የፀጥታ አካላት በጋራ በመሥራታቸው በዓሉ ያለምንም የፀጥታ ስጋት በሰላም መከበሩ ተናግረዋል።

ኮሚሽነር ነብዩ አክለው ነገ የሚከበረው የቃና ዘገሊላ በዓልም በሰላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ ሁሉም አካላት በተቀናጀ አግባብ እንዲሰሩ አሳስበዋል።

ከዚህም ባሻገር በክልሉ ከበዓሉ ዋዜማ ጀምሮ የትራፊክ አደጋ አለመድረሱን ገልጸው፣ ለዚህም አሽከርካሪዎች በሙሉ ኃላፊነት በጥንቃቄ ማሽከርከራቸው አስተዋፅኦ አድርጓዋል ብለዋል።

የጥምቀት በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ የፀጥታ አካላት፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶች፣ አሽከርካሪዎችና መላዉ ሰላም ወዳድ የክልሉን ህዝብ ላደረጉት አስተዋጽኦ ኮሚሽነር ነብዩ አመስግነዋል።

በተመሳሳይ ዜና የደቡብ ክልል የከተራና ጥምቀት ክብረ በዓል በሰላም ተጠናቅቆ ታቦታቱ ወደየመጡበት አብያተ ክርስቲያናት መለሳቸውን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ዓለማየሁ ማሞ ገልጸዋል።

በዓሉ ያለምንም የፀጥታና ደህንነት ስጋት እንዲከበር የፖሊስ ኃይል ከህዝቡ ጋር በመቀናጀት ከፍተኛ ስራ መስራቱን አስረድተዋል።

በተለይ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን ጨምሮ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ ከፀጥታው ኃይል ጎን በመሆን ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።

በዓሉ በሲዳማ ክልል በዓሉ በሰላም እንዲከበር የክልሉ ፖሊስ በየደረጃው ከሚገኙ የፀጥታ አካላት ጋር በጋራ በመስራቱ ያለምንም የፀጥታ ስጋት መከበሩን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ተስፋዬ ቱንጋሞ አስታውቀዋል።

በዚህም ታቦታቱ ወደ የመጡበት ደብሮች በሰላም መመለሳቸውን ኮሚሽነር ተስፋዬ ገልጸው፣ የበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በዓሉ ያለምንም የፀጥታ ስጋት እንድከበር የድርሻቸውን መወጣታቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም