በአገራችን አሁን የተገኘውን ሰላም ዳር ለማድረስ ሁሉም አካል ተባብሮና ተጋግዞ በቁርጠኝነት መስራት አለበት--ሊቀ ሊቃውንት ስመዓ ኮነ መላክ

37

ጥር (ኢዜአ) 11/2015 በአገራችን አሁን የተገኘውን ሰላም ዳር ለማድረስ ሁሉም አካል ተባብሮና ተጋግዞ በቁርጠኝነት መስራት እንዳለበት የባህር ዳር ሃገረ ስብከት የሊቃውንት መምሪያ ሃላፊ ሊቀ ሊቃውንት ስመዓ ኮነ መላክ ገለጹ።

በከተማዋ የሃይማኖት አባቶችና በርካታ ቁጥር ያላቸው ምዕመናን በተገኙበት የጥምቀት በዓል በድምቀት ተከብሯል።

በበዓሉ ላይ የባህር ዳር ሃገረ ስብከት የአራቱ ጉባኤያት መምህርና የሊቃውንት መምሪያ ሃላፊ ሊቀ ሊቃውንት ስመዓ ኮነ መላክ ባስተላለፉት መልዕክት አንዳሉት፣ የጥምቀት በዓል መጽሀፍ ቅዱሳዊ ስርዓትን መሰረት አድርጎ በየዓመቱ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚከበር ነው ።

በዓሉ ህዝበ ክርስቲያኑ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ሄዶ በዮሐንስ እጅ የተጠመቀበትን እለት በየዓመቱ በመዘከር ራሱን ከክፋት፣ ከጥላቻና ከሴራ በማጽዳት በንስሃ የሚታደስበት መሆኑንም ገልጸዋል።

"የሰው ልጅ በእዚህች ምድር ሲኖር ተፈቃቅሮ፣ ተከባብሮና ተደጋግፎ በአብሮነትና በአንድነት መኖርን እንዳለበትም ፈጣሪ አስተምሮናል" ብለዋል።

"ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኢትዮጵያውን መልካም እሴት እየተሸረሸረ መጥቷል" ያሉት ሊቀ ሊቃውንቱ፣ "ከዚህ ችግር መዳኛው መንገድ እንደ ፈጣሪ ትዕዛዝ ተፈቃቅሮ መኖር ነው" ብለዋል።

የጥምቀት በዓል ከሃይማኖታዊ ክዋኔው በሻገር ለአብሮነት መጠናከር፣ ለቱሪዝምና ሌሎች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማቶች ፋይዳው የጎላ በመሆኑ ጠብቆ ማቆየት የሁሉም ሃላፊነት እንደሆነም አስገንዝበዋል።

ምዕመኑ በሃይማኖት መሪዎች የሚሰጠውን ትምህርት ወደግል ህይወቱ ወስዶ በመተግበር ሁሌም እርስ በርስ ተፈቃቅሮና ተከባብሮ መኖር እንዳለበትም አሳስበዋል።

በዓሉን አቅመ ደካሞችን፣ ድሆችን እና በወቅታዊ ችግሮች ምክንያት የተጎዱ የህብረተሰብ ክፍሎችን በመደገፍ ማክበር እንደሚገባም ሊቀ ሊቃውንት ስመዓ ኮነ ተናግረዋል።

"ያለሰላም ሃይማኖታዊ በዓል ማክበርም ሆነ ሌሎች የግልና የጋራ ክዋኔዎችን መፈጸም አስቸጋሪ ነው" ያሉት ሊቀ ሊቃውንቱ፣ "ሁላችንም ለሰላም ዘብ መቆም አለብን" ብለዋል።

በአገራችን አሁን የሰፈነውን ሰላም ዳር ለማድረስ ሁሉም አካል ተባብሮና ተጋግዞ በቁርጠኝነት መስራት እንዳለበት ነው ያሳሰቡት።

የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ በማክበር ለቱሪዝም ልማት እንዲውልና ሀገርም ከዘርፉ እንድትጠቀም በትኩረት መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም