የጥምቀት በዓልን ስናከብር ሰላምና አንድነታችንን በማጽናት ሊሆን ይገባል- ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ - ኢዜአ አማርኛ
የጥምቀት በዓልን ስናከብር ሰላምና አንድነታችንን በማጽናት ሊሆን ይገባል- ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ
አዲስ አበባ (ኢዜአ)ጥር 11/2015 የጥምቀት በዓልን ስናከብር ሰላምና አንድነታችንን በማጽናት ሊሆን ይገባል ሲሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ አሳሰቡ።
በአዲስ አበባ ጃንሜዳ ጥምቀተ-ባህር በተካሄደው በዓለ-ጥምቀትም ብጹዓን አባቶች፣ የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ ቀጀላ መርዳሳ፣ የአገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች እንዲሁም የእምነቱ ተከታዮች በተገኙበት ሥርዓቱን ጠብቆ በድምቀት ተከብሯል።
በበዓሉ አከባበር ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፤ ፈጣሪ የሚፈልገውን በጎ ነገር ማድረግ እና ለመልካም ነገር መዘጋጀት እንደሚገባም ተናግረዋል።
ከአሁን በፊት ከደረሱ ጥፋቶች ትምህርት በመውሰድ ለቀጣይ አገራዊ ሰላምና አንድነት ሁሉም የበኩሉን ኃላፊነት መወጣት እንዳለበትም አሳስበዋል።
የጥምቀት በዓል ክብሩ ተጠብቆ በሰላም እና በፍቅር እንዲከበር ላደረጉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፀጥታ አካላት፣ ወጣቶች፣ ካህናትና ህዝቡ ምስጋና አቅርበዋል።
የጥምቀት በዓልን ስናከብር ሰላምና አንድነታችንን በማጽናት የኢትዮጵያን እድገትና ህልውና አጠናክረን የምንገነባበት ሊሆን ይገባል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንደ ጥምቀት ያሉ ሕዝባዊ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።
አብሮነትን በማጠናከር አንድነትን ለማስቀጠል የጥምቀት በዓልን ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴት መላበስ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያዊያንን ደስታና ሰላም ለማጽናት፣ አብሮነትን ለማጠንከር፣ ፍቅርና አንድነትን ለማጽናት የጥምቀት በዓል አከባበር አንዱ እሴት መሆኑን ጠቅሰዋል።
የጥምቀት በዓል ማህበራዊ ትስስርን የሚያጠናክር ድንቅ ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴት ነው ያሉት ደግሞ የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ ቀጄላ መርዳሳ ናቸው።
የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ ጥበቃና እንክብካቤ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያን ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊና ታሪካዊ እሴቶች ለአገር ኢኮኖሚ ግንባታ እንዲውሉ ሚኒስቴሩ በትኩረት እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ሥርዓቱን ጠብቆ በሰላም እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የጸጥታ አካላት፣ በጎ-ፈቃደኛ ወጣቶችና አጠቃላይ ህብረተሰቡን አመስግነዋል።