በጅግጅጋ፣ ጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ፣ ሐረሪ ክልል እና ድሬደዋ የጥምቀት በዓል በሰላም ተከብሯል-ፖሊስ - ኢዜአ አማርኛ
በጅግጅጋ፣ ጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ፣ ሐረሪ ክልል እና ድሬደዋ የጥምቀት በዓል በሰላም ተከብሯል-ፖሊስ

ጅግጅጋ፤ ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ፣ ሐረሪ (ኢዜአ) ጥር 11 ቀን 2015- በሶማሌ ክልል የጅግጅጋ ከተማ ፣ በጋምቤላ ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ሁሉም አካባቢዎች ፣ በሐረሪ ክልል እና በድሬደዋ የጥምቀት በዓል ያለምንም ችግር በሰላም ተከብሮ መጠናቁቁን ፖሊስ አስታወቀ።
የጅግጅጋ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ አዛዥ ምክትል ኮማንደር አንወር መሀመድ አህመድ ፤ በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ አስቀድሞ ከወጣቶች ጋር በመስራታችን ውጤታማ አደርጎናል ብለዋል።
የበዓሉ ስነ-ስርዓት ያለምንም ችግር እንዲጠናቀቅ አስተዋፅኦ ላበረከቱ የከተማው ነዋሪዎች ምስጋና አቅርበዋል።
በሌላ በኩል የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ሙሉጌታ ሩት፤ በዓሉ በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ያለምንም የጸጥታ ችግር በሰላም ተጠናቋል ብለዋል።
ህዝበ ምዕመኑ በክብረ በዓሉ ያሳየውን ትብብርና ጨዋነት በእጅጉ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።
በጋምቤላ ከተማ በቀጣይም ቃና ዘገሊላን ጨምሮ በተከታታይ ለአራት ቀናት በሚቆየው ክብረ በዓል ህዝበ ምዕመኑ ያሳየውን ትብብርና ጨዋነት አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።
በተያያዘ ዜና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሃሩን ኡመር ፤ በክልሉ ለበዓሉ ስኬት የጋራ ግብረሃይል ተቋቁሞ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።
ህብረተሰቡ መረጃ በመስጠት ብቻ ሳይሆን በደረጃው ከሚገኙ የጸጥታ ሃይሎች ጋር አብሮ በመስራት ጭምር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።
በዚህም በዓሉ በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ያለምንም የጸጥታ ችግር በሠላም ተከብሮ መጠናቀቁን ኮሚሽነር ሃሩን ኡመር አስታውቀዋል።
እንዲሁም የሃረሪ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ነስሪ ዘከርያ ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ የከተራና የጥምቀት በዓል የህዝቡን አብሮነትና አንድነት ባሳየ ደማቅ ሥነ-ሥርዓት በሰላም ተከብሮ ተጠናቋል።
በዓሉ በሰላም እንዲከበር አስተዋጾ ላደረጉ የጸጥታ አካላት፣ወጣቶችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ምስጋና አቅርበዋል።
በሌላ ዜና የድሬደዋ አስተዳደር ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ የለውጥ ና የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ገመቹ ካቻ ለኢዜአ እንደተናገሩት ፤ የከተራና የጥምቀት በዓላት ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላምና በደመቀ ሁኔታ ተከብረዋል ።

የአስተዳደሩና የፌደራል የፀጥታ አካላት በየደረጃው ከሚገኘው ማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስና የወጣቶች አደረጃጀት ጋር በመቀናጀት ያከናወኗቸው ተግባራት በዓላቱ በሰላም እንዲጠናቀቁ አስችሏል ብለዋል።
ለበዓሉ ሰላምና ማማር የእስልምና ኃይማኖት ተከታዮችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ያደረጉት ድጋፍና መተባበር የድሬዳዋ ህብረ ብሔራዊ አንድነት የተንፀባረቀበት መሆኑን ኮማንደር ገመቹ ጠቅሰዋል።