ቀጥታ፡

የጥምቀት በዓልን ሃይማኖታዊ እሴትና የአገር ሃብትነቱን ጠብቆ ማስቀጠል የጋራ ሥራችን ሊሆን ይገባል - የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን አማኞች

አዲስ አበባ (ኢዜአ)ጥር 11/2015 የጥምቀት በዓልን ሃይማኖታዊ እሴትና የአገር ሃብትነቱን ጠብቆ ማስቀጠል የጋራ ሥራችን ሊሆን ይገባል ሲሉ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን አማኞች ገለጹ፡፡

በኢትዮጵያ በአደባባይ ከሚከበሩ ሃይማኖታዊ በዓላት መካከል አንዱ ጥምቀት ነው፡፡

የጥምቀት በዓል በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከከተራ ጀምሮ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓቶች በድምቀት ተከብሯል።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የጥምቀት በዓልን በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓቶች በልደታ ማሪያም ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን አክብራለች፡፡

የበዓሉን አከባበር አስመልክቶ ኢዜአ ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን አማኞች የጥምቀት በዓልን ሃይማኖታዊ እሴትና የአገር ሃብትነቱን ጠብቆ ማስቀጠል የጋራ ሥራችን ሊሆን ይገባል ብለዋል።

በክብረ-በዓሉ ላይ አግኝተን ካነጋገርናቸው መካከል ወይዘሪት ረድኤት ደንድር፤ ጥምቀት ከሃይማኖታዊ ሥነ- ሥርዓቱ ባለፈ የአገር ሃብት በመሆኑ ጠብቀን ለትውልድ ማስተላለፍ አለብን ብላለች።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ ማስረሻ አውላቸው በበኩላቸው፤ ጥንት አያቶች በዓላቶች እሴታቸውን ጠብቀው እንዲከበሩ አድርገው አቆይተውልናል እኛም የማስቀጠል አደራ አለብን ብለዋል።

ሕዝበ-ክርስቲያኑ ከፈጣሪ የተሰጠውን ሃይማኖታዊ ፀጋ በማስቀጠል ለትውልድና ለአገር በሚጠቅም መልኩ ማስተላለፍ ይገባል ሲሉ አቶ ሲሳይ ካሳ ገልጸዋል።

የሰላም ጉዳይ የሁሉ ነገር መሰረት በመሆኑ አብሮነት፣ ፍቅር፣ መተባበርና የአገር አንድነትን እናጠንክር ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም