የምናከብራቸው በዓላት የአብሮነታችን ማሳያና የመተባበራችን ተምሳሌት ሆነው ሊቀጥሉ ይገባል- ሊቀ-ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል - ኢዜአ አማርኛ
የምናከብራቸው በዓላት የአብሮነታችን ማሳያና የመተባበራችን ተምሳሌት ሆነው ሊቀጥሉ ይገባል- ሊቀ-ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል
አዲስ አበባ(ኢዜአ) ጥር 11/2015 የምናከብራቸው በዓላት የአብሮነታችን ማሳያና የመተባበራችን ተምሳሌት ሆነው ሊቀጥሉ ይገባል ሲሉ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ-ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል ተናገሩ፡፡
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የጥምቀት በዓልን በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓቶች በልደታ ማሪያም ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን አክብራለች፡፡
በዓሉ በቅዳሴ፣ በፀሎትና በዝማሬ የተከበረ ሲሆን፤ የሃይማኖት አባቶች፣ የእምነቱ ተከታዮችና እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ-ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል፤ በእለቱ ባስተላለፉት መልዕክት ሕዝበ-ክርስቲያኑ የጥምቀት በዓልን ሲያከብር እርስ በርስ በመከባበርና በመረዳዳት ሊሆን ይገባል ብለዋል።
የምናከብራቸው በዓላት የአብሮነታችን ማሳያና የመተባበራችን ተምሳሌት ሆነው ሊቀጥሉ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።
ከጥንት አያቶቻችን የተረከብናቸውን ክብረ-በዓላትና መልካም እሴቶች በማስቀጠል አንድነታችንን ማጠንከር አለብን ብለዋል።
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ጸሐፊ ዶክተር አባ ተሾመ ፍቅሬ በበኩላቸው፤ ሕዝበ- ክርስቲያኑ በዓሉን ሲያከበር ከፈጣሪ የተሰጠውንም ፀጋ በማስታወስ ጭምር ሊሆን ይገባል ብለዋል።
ከበዓሉ ታዳሚዎች መካከል አቶ ኃይሉ መንዲዳ፤ በዓሉን በጋራና በደስታ በማክበራቸው መደሰታቸውን ጠቅሰው፤ የሰላምና አብሮነት እሴቶቻችንን አጠናክረን መቀጠል አለብን ሲሉ ተናግረዋል።