የጦርነትን ጉዳትና የሚያስከትለውን ኪሳራ አይተነዋል፤ ሁላችንም የምንሻው ሰላም፣ ፍቅርና አብሮነትን ብቻ ነው- የአክሱም ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የጦርነትን ጉዳትና የሚያስከትለውን ኪሳራ አይተነዋል፤ ሁላችንም የምንሻው ሰላም፣ ፍቅርና አብሮነትን ብቻ ነው- የአክሱም ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች
አዲስ አበባ ጥር 11 ቀን 2015(ኢዜአ) "የጦርነትን ጉዳትና የሚያስከትለውን ኪሳራ አይተነዋል፤ ሁላችንም የምንሻው ሰላም፣ ፍቅርና አብሮነትን ብቻ ነው" ሲሉ የአክሱም ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ።
ነዋሪዎቹ በታሪካዊቷ አክሱም ከተማ ከሁለት ዓመታት በኋላ የጥምቀት በዓልን በደማቅ ሁኔታ በማክበራቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።
በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረው ግጭት በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና አጠቃላይ በሕዝቡ አኗኗር ላይ ውስብስብ ችግሮችን ማስከተሉ ይታወቃል።
በዚህም በተለይም በዓላትን ተሰባስቦና በጋራ ተደስቶ ለማክበር የነበረው የሰላም እጦት ፈተና እንደነበር በርካቶች ይናገራሉ።
የጦርነትና ግጭት ጉዳይ በሰላማዊ መፍትሔ እልባት ማግኘት እንዳለበት መንግሥት ጽኑ አቋም ይዞ በመስራቱ በሰሜን ኢትዮጵያ የሰላም አየር መንፈስ ከጀመረ ወራቶች እየተቆጠሩ ነው።
ከሰላም ስምምነቱ በኋላ የጥምቀት በዓልን በደማቅና በተረጋጋ ሁኔታ በማክበራቸው የአክሱም ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።
የኢዜአ ሪፖርተር በአክሱም ከተማ ተገኝቶ የከተራና የጥምቀት በዓላት አከባበር ድባብ ምን እንደሚመስል በመቃኘት ነዋሪዎችንም አነጋግሯል።
የጥምቀት በዓል ላለፉት ሁለት ዓመታት በአክሱም ከተማ "ተከበረ ለማለት አያስደፍርም" የሚሉት ነዋሪዎቹ አሁን ላይ በአካባቢው በሰላም ተንቀሳቅሰው በማክበራቸው ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ተናግረዋል።
የዘንድሮው የጥምቀት በዓል ዘመድ ከዘመዱ የተገናኙበት፣ አምላክን ማመስገን የቻሉበት ክብረ-በዓል መሆኑንም ነዋሪዎቹ ይናገራሉ።
የጦርነትን ጉዳትና የሚያስከትለውን ኪሳራ አይተነዋል የሚሉት ነዋሪዎቹ፤ ሁላችንም የምንሻው ሰላም፣ ፍቅርና አብሮነትን ብቻ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የሰላም ስምምነቱን ተከትሉ የተፈጠረው ሰላም በዘላቂነት እንዲቀጥል የዘወትር ጸሎትና ምኞታችን ነው ብለዋል።