በደምበል ሀይቅ ላይ የጥምቀት በዓል ለየት ባለመልኩ ደምቆ እየተከበረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በደምበል ሀይቅ ላይ የጥምቀት በዓል ለየት ባለመልኩ ደምቆ እየተከበረ ነው
ባቱ ጥር 10/2015 በባቱ ደምበል ሀይቅ ላይ የጥምቀት በዓል ለየት ባለመልኩ ደምቆ እየተከበረ ይገኛል።
በጥምቀተ ባህሩ ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሀይማኖት አባቶች ስርዓተ ጥምቀቱን እያከናወኑ፤ ለምዕመኑም ኃይማኖታዊ ትምህርት እያስተላለፉ ነው።
የባቱ ከተማ ከንቲባ አቶ ገዛኸኝ ደጀኔ በበዓሉ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት በደንበል ሀይቅ የጥምቀት በዓል በአይነቱ ልዩ ሆኖ በደማቅ ሁኔታ የሚከበር ነው ብለዋል።
ሀይቅ ላይ ተጀምሮ ሀይቅ ላይ የሚጠናቀቀው የደንበል ሀይቅ የጥምቀት በዓል አከባበር እጅግ ማራኪና በርካታ ቱሪስቶች የሚታደሙበት መሆኑንም አክለዋል።
ይህንኑ መነሻ በማድረግ የባቱ ከተማ አስተዳደር ሀይቁን ማልምት መጀመሩን ገልጸው በልማት ስራው በርካታ የአካባቢው ወጣቶች የስራ እድል ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የከተማ አስተዳደሩ የጀመረውን ሀይቁን የማልማት ስራ ሁሉም በሚችለው እንዲደግፍ ጠይቀው ይህ ሲሆን ሀይቁ ተጨማሪ ውበት መሆን እንደሚችል ተናግረዋል።
የበዓሉ ታዳሚዎች በበኩላቸው ጥምቀትን በዚህ መልኩ ማክበራቸው እንዳስደሰታቸውና ልዩ ስሜት እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል።
የደንበል ሀይቅ የጥምቀት በዓል የተለየ መልክ ቢኖረውም እምብዛም ትኩረት ሳይሰጠው የቆየ መሆኑን ጠቁመው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን በርካታ ሰዎች እየታደሙበት ይገኛሉ ብለዋል።
በሀይቁ ላይ ከሚገኙ ደሴቶች ተሰባስበው በባቱ ከተማ ዳርቻ ያደሩት ታቦታቱ በጀልባና በታንኳ ታጓጉዘው ወደየ አብያት ክርስትያናቱ ይመለሳሉ።