በምንጃር ሸንኮራ የጥምቀት በዓልን ቱሪዝሙን ለማነቃቃትና ለኢኮኖሚ ጥቅም ማዋል ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በምንጃር ሸንኮራ የጥምቀት በዓልን ቱሪዝሙን ለማነቃቃትና ለኢኮኖሚ ጥቅም ማዋል ይገባል

ደብረ ብርሀን (ኢዜአ) ጥር 11/ 2015 ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ በየዓመቱ በድምቀት የሚከበረውን የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊና ባህላዊ ትውፊቱን በመጠበቅና በማስተዋወቅ ቱሪዝሙን ለማነቃቃትና ለኢኮኖሚ ጥቅም ማዋል ይገባል ሲሉ የበዓሉ ታዳሚዎች ገለጹ።
በወረዳው የራንቡቲ አምሳለ ዮርዳኖሰ እየተከበረ ባለው የጥምቀት በዓል ለመታደም ከሐረር ከተማ የመጡት አቶ ፍቃዱ ከፍሌ እንዳሉት፣ በምንጃር ሸንኮራ በሚከበረው የጥምቀት በዓል ሲታደሙ ዘንድሮ 15 ዓመታቸው ነው።

ለበዓሉ 44 ታቦታት ከያሉበት ወጥተው በአንድ ላይ በጥምቀተ ባህሩ ማደራቸውና በዓሉ ሀይማኖታዊና ባህላዊ ትውፊቱን ጠብቆ በተለየ መልኩ መከበሩ በየዓመቱ ወደአካባቢው መጥተው በዓሉን ለማክበር እንዳነሳሳቸው ገልጸዋል።
ከእዚህ በተጨማሪ የአካባቢው መልክአምድራዊ አቀማመጥና የህብረተሰቡ የእንግዳ ተቀባይነት ባህል በመሳብ በየዓመቱ በዓሉን እያከበሩ መሆኑን ተናግረዋል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በምንጃር ሸንኮራ በሚከበረው የጥምቀት በዓል ከሌላ አካባቢ የሚመጡ እንግዶች ቁጥር እየጨመረ እንደሆነ መታዘባቸውንና ይህም ቱሪዝሙ ለማነቃቃት ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል።
በመሆኑም የአካባቢውን የጥምቀት በዓል አከባበር ይበልጥ በማልማትና በማስተዋወቅ ቱሪዝሙን ለማሳደግና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳውን ለማጎልበት በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
አቶ ቦጋለ በየነ የተባሉ ሌላው የበዓሉ ታዳሚ በበኩላቸው፣ በወረዳው በራንቡቲ አምሳለ ዮርዳኖሰ በየዓመቱ የሚከበረው የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊና ባህላዊ ትውፊትን ጠብቆ በመከበሩ መስህብነቱ የጎላ ነው።
የበዓሉን ባህላዊ ትውፊትና ሃይማኖታዊ አከባበር በሚገባ በመጠበቅና በማስተዋወቅ የውጭና የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችን በመሳብ የሃብት ማግኛ ለማድረግ ጠንክሮ መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።
"ከትናንት የሰላም እጦት ድባብ ወጥተን ዛሬ የከተራና የጥምቀት በዓልን በሰላም፣ በአብሮነትና በፍጹም መረጋጋት ለማክበር በመቻላችን ደስተኛ ነኝ፤ ለእዚህም እንደሀገር የሰፈነው ሰላም አስተዋጾው የጎላ ነው" ሲሉም አቶ ቦጋለ አክለዋል።
በቀጣይ የምንጃር ሸንኮራን የጥምቀት በዓል ለሀገራዊ አንድነት፣ ለህዝቦች ትስስር፣ ለቱሪዝም መነቃቃትና ለኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዲውል ለማስተዋወቅ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ አመልክተዋል።
ከእዚህ በተጨማሪ የውጭና የአገር ውስጥ ቱሪስቶች በስፋት ወደ አካባቢው መጥተው እንዲያከብሩ እንግዶችን ለማስተናገድ የሚያስችሉ መሰረት ልማቶችን ቀድሞ ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግም መክረዋል።
በበዓሉ እለት የአካባቢው ማህበረሰብ ባህላዊ አልባሳት፣ የጸጉር አሰራር፣ ባህላዊ ዘፈን፣ ሆታና ጭፈራ የተለየ ትዕይንት በመሆኑ ቱሪስቶችን ለመሳብ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርም ተናግረዋል።
የምንጃር ሸንኮራ ወረዳ የባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ሀላፊ ወይዘሮ በላይነሽ ተሻለ በወረዳው የሚከበረው የጥምቀት በዓል በአይነቱ የተለየ ድምቀትና ድባብ እንዳለው ገልጸዋል።
ይህም ወደአካባቢው መጥተው በዓሉን የሚታደሙ ምዕመናንና እንግዶች ቁጥር ከጊዜ ወደጊዜ እንዲጨምር ማድረጉን ነው የተናገሩት።
በወረዳው ያሉ የቱሪስት መስህብ ሥፍራዎችንና የጥምቀት በዓልን በሚገባ አልምቶ ለማስተዋወቅ ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑንም አስረድተዋል።
በእዚህም አካባቢውን ለመጎብኘትም ሆነ ለጥምቀት በዓል የሚመጡ እንግዶች የማረፊያ ስፍራ፣ የምግብና መጠጥ አገልግሎት በየደረጃቸው እንዲያገኙ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተለይ ቱሪስቱን የሚመጥኑ ሆቴሎች፣ ምግብ ቤቶችና ሌሎች የአገልግሎት መስጫዎች በስፋት እንዲገነቡ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩ ወይዘሮ በላይነሽ አመልክተዋል።
አካባቢው አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት ያለበት መሆኑን የገለጹት ሃላፊዋ፣ ወደአካባቢው መጥተው በቱሪዝም ዘርፍ መዋዕለንዋያቸውን ለሚያፈሱ ባለሀብቶች ምቹ ሁኔታ መኖሩንም ጠቁመዋል።