ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ አስደናቂ የበዓላት አከባበር፣ እምቅ የተፈጥሮ ጸጋና ምቹ የአየር ንብረት በእጅጉ ተደንቀናል

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 11/2015 የኢትዮጵያ አስደናቂ የበዓላት አከባበር፣ እምቅ የተፈጥሮ ጸጋና ምቹ የአየር ንብረት በእጅጉ መደነቃቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው የውጭ አገር ቱሪስቶች ገለጹ።

በአዲስ አበባ ጃንሜዳ የከተራና የጥምቀት በአልን ለመታደም ከተለያዩ የአለም አገራት የመጡ በርካታ ቱሪስቶች ተገኝተዋል።

ከጎብኝዎቹ መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ አገራት ዜጎች በኢትዮጵያ ቆይታቸው መደሰታቸውንና የማይረሳ ትውስታ መሰነቃቸውን ይናገራሉ።

በጥምቀት ዋዜማ በሚከናወነው የከተራ በዓል በተመለከቱት ሃይማኖታዊና ባህላዊ ስርአት መደነቃቸውንም ጎብኝዎቹ ገልጸዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ አስደናቂ የበዓላት አከባበር፣ እምቅ የተፈጥሮ ጸጋና ለመኖር የሚመች የአየር ንብረቷ አስደንቆናል ብለዋል።

በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የባህልና ሳይንስ ተቋም (ዩኔስኮ) በአለም ቅርስነት የተመዘገበው የጥምቀት በአል አስገራሚ ሃይማኖታዊ ይዘት እንዳለው መመልከታቸውንም ገልጸዋል።

ከአሜሪካ የመጣው ማዬር አሜር በከተራ በአል ላይ ሲታደም የመጀመሪያው መሆኑን በመግለጽ የህዝብ መሰባሰብ፣ አንድነት፣ ሃይማኖታዊ ስርአትና ሌሎች በበአሉ ላይ የሚስተዋሉ ሁነቶች የተለየ ስሜት ፈጥረውብኛል ብሏል።

ከእስፔን የመጣችው ጎብኝ አይሪስ ኮራ፤ ላሊበላን ጨምሮ ሌሎች ቦታዎችን ተዘዋውራ መጎብኘቷን በመግለጽ የኢትዮጵያ አስገራሚና አስደናቂ ሃብቶች አድንቃለች።

በጥምቀት በአል ላይ ሲታደም የመጀመሪያው የሆነው እንግሊዛዊው አንቶኒ ሃርሞንተን በበኩሉ ኢትዮጵያ በብዙ ነገሮች የታደለችና ውብ አገር መሆኗን ተረድቻለሁ ብሏል።

የኢትዮጵያዊያን እንግዳ አቀባበል፣ የሚያሳዩት ቤተሰባዊነት፣ መስተንግዷቸውና አጠቃላይ የሚሰጡት አክብሮች የማይረሳ ትዝታ አሳድሮብኛል ሲል ተናግሯል።

የኢትዮጵያ አስደናቂ ክብረ በዓል፣ የተፈጥሮ ጸጋና አጠቃላይ ውበት የአለም ቱሪስቶች እንዲጎበኙት መልእከቱን አስተላልፏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም