ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ያሉ ቱባ ኃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶችን ለዓለም በማስተዋወቁ ረገድ ትልቅ አደራ አለብን-ዳያስፖራዎች

አዲስ አበባ ኢዜአ ጥር 11/2015 በኢትዮጵያ ያሉ ቱባ ኃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶችን ለዓለም በማስተዋወቁ ረገድ የዳያስፖራው ማህበረሰብ በልዩ ትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ኢዜአ ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች ገለጹ።

የከተራና ጥምቀት በዓል በጃንሜዳ ደማቅ በሆነ ኃይማኖታዊ ሥነ ስርዓት ተከብሯል።

በበዓሉ አከባበር ላይ የተለያዩ የውጭ አገራት ዜጎች እና ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራዎች ተግኝተዋል። 

በበዓሉ ላይ ከታደሙት መካከል በፈረንሳይ ፓሪስ ለረጅም ዓመታት የኖሩት የቀድሞ ብሄራዊ ቡድን እግር ኳስ ተጫዋች ግርማ ሳሬ አንዱ ናቸው።  

በአዲስ አበባ ጃንሜዳ በልጅነታቸው ከእድሜ አቻዎቻቸው ጋር በማክበር የማይረሳ ጊዜ ማሳለፋቸውን አስታውሰው ከረጅም ዓመታት በኋላ በአዲስ አበባ ተገኝተው ጥምቀትን በማክበራቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።  

በውጭ ያሉ ኢትዮጵያዊያን የተለያዩ ኃይማኖታዊና ህዝባዊ በዓላትን ከወገኖቻቸው ጋር ቢያሳልፉ ከሚያገኙት ደስታ ባለፈ መረጃ ሰንደው አገራቸውን ለማስተዋወቅ ጥሩ አጋጣሚ መሆኑን ይናገራሉ። 

በመሆኑም እርሳቸውን ጨምሮ በየትኛውም አለም የሚኖሩ ዳያስፖራዎች በኢትዮጵያ ያሉ ቱባ ኃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶችን ለዓለም በማስተዋወቁ ረገድ በትኩረት መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል። 

የበርካታ ሃብቶችና ቅርሶች ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ የዓለም ቱሪስቶችን ቀልብ የምትገዛ በመሆኗ እንድትጎበኝ ሁላችንም ማስተዋወቅ አለብን ብለዋል። 

በዚህ ጉዳይ በተለይም የዳያስፖራው ማህበረሰብ ትልቅ አደራና ሃላፊነት አለበት ሲሉም ተናግረዋል። 

በደቡብ አፍሪካ ለ16 ዓመታት ቆይተው ወደ ኢትዮጵያ የመጡት አቶ ዮሃንስ አመንቴ በበኩላቸው ከረጅም ዓመታት በኋላ በጃንሜዳ ተገኝቼ በዓሉን በማክበሬ ጥልቅ ደስታ ተሰምቶኛል ብለዋል። 

በውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ ኃይማኖቱን እና ትውፊቱን ለውጭ አገር ዜጎች በዝርዝር ማስረዳት መቻሉ ጎብኚዎችን ለመሳብ ቁልፍ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል።

ዳያስፖራው አገሩን ለማስተዋወቅ ኢትዮጵያ ምን ምን ሃብቶች አሏት? የትኞቹ ጎልተው ቢወጡ ጠቃሚ ይሆናል የሚለው ላይ በቂ መረጃ ሊኖረው እንደሚገባም ነው አጽንኦት የሰጡት። 

በኢትዮጵያ ያሉ የቱሪስት መስህቦችን ለማስተዋወቅ በውጭ ያሉ የዳያስፖራ ማህበራት የድርሻቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም