በሀዋሳ ከተማ የጥምቀት በዓል እየተከበረ ነው

ሀዋሳ ጥር 11/2015 (ኢዜአ) በሀዋሳ የጥምቀት በዓል እየተከበረ ይገኛል ።

በደብረ ምጥማቅ መድኃኔዓለም ቤተክስትያን እየተካሄደ ባለው የጥምቀት ክብረ በዓል ላይ  የሲዳማ ፣የጌዴኦ ፣አማሮና ቡርጂ እንዲሁም የምዕራብ አርሲ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ ተገኝተዋል ።

እንዲሁም የሲዳማ ሀገረ ስብከት ስራ አስኪያጅ  መጋቤ ጥበባት ቀሲስ ሞላልኝ መርጊያ ሌሊት በማህሌትና ቅዳሴ ሥርዓት ሲያመሰግኑ ያደሩት የቤተክርስቲያኒቱ ሊቃውንትና በርካታ ምዕመናን ተገኝተዋል ።

ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ ቃለ ምዕዳን እና ቡራኬ በሰጡበት ወቅት ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በባህረ ዮርዳኖስ የተጠመቀው የሰው ልጆችን የዕዳ ደብዳቤ በመደምሰስ ከባርነት ቀንበር ነፃ ለማውጣት ነው ብለዋል ።

በክርስቶስ ያገኘነውን ነፃነታችንን ጠብቀን ለመኖር  ራሳችንን መግዛትና ከክፋት ማራቅ ይጠበቅብናል ነው ያሉት ።

ሠላምና ለሰው ልጆች ሁሉ ፍቅርን መስጠትን ዋንኛ የሕይወት መርህ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል ።

ሥልጣን፣ ዝናና ሀብትን በመጠቀም ሌሎችን ከመበደል መራቅ በተለይ ለተቸገሩ ዜጎች የሚራራ ልብ ያስፈልገናል ብለዋል ።

በአቋራጭ ለመክበር ከሚደረግ ጥረት ከሌብነት ፣ ከሀሰት ፣ ከመለያየትና እርስበርስ ከመጨካከን ራስን ማቀብ ያሻል ነው ያሉት ።

ኢትዮጵያ የቀደመ የአብሮነትና አንድነት እሴቶቿ ተጠብቀው ፅኑ ሀገር ሆና እንድትቀጥል እርስ በርስ ከመገፋፋትና ከመጠላላት ይልቅ መከባበርና መዋደድ እንደሚገባም አስገንዝበዋል ።

የሲዳማ ሀገረ ስብከት ስራ አስኪያጅ  መጋቤ ጥበባት ቀሲስ ሞላልኝ መርጊያ የጥምቀት በዓል ከሐይማኖታዊ አስተምህሮቱ ባሻገር የኢትዮጵያን አንድነትና ትሥሥር የሚያጠናክሩ ማህበራዊ ኩነቶች በውስጡ መያዙንጠቅሰዋል ።

የሀገርን ገፅታ በበጎ መልኩ በማጉላት ከፍተኛ ሚና እዳለው ተናግረዋል ።

የዓለም ቅርስ የሆነው ይህ በዓለ ጥምቀት ሐይማኖታዊና ማህበራዊ ትውፊቶቹ ተጠብቀው እንዲቀጥሉ ብሎም ኢትዮጵያ ከቱሪዝም ዘርፍ የምታገኘው ጥቅም እየላቀ እንዲሄድ በትብብር መስራት እደሚያስፈልግ አስረድተዋል ።

በበዓሉ አከባበር ላይ የተለያዩ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችም ታድመዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም