ቀጥታ፡

በተፈጠረው ሰላምና መረጋጋት በትግራይ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የዘንድሮው የጥምቀት በዓል በደማቅ ሁኔታ እየተከበረ ነው

አዲስ አበባ ጥር 11/2015 (ኢዜአ) በተፈጠረው ሰላምና መረጋጋት በትግራይ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የጥምቀት በዓል በደማቅ ሁኔታ እየተከበረ መሆኑን የርዕሰ አድባራት ወገዳማት አክሱም ፂዮን ማርያም አስተዳዳሪ ቆሞስ ንቡረ ዕድ አባ መሀሪ ሀብቴ ተናገሩ።

በአደባባይ የሚከበረው የጥምቀት ክብረ በዓል ከኃይማኖታዊ በዓልነቱ ባሻገር ባህላዊ እሴቱን በጠበቀና ባማረ መልኩ እየተከበረ ቀጥሏል።

የጥምቀት በዓል ከአገራዊ ሃብትነቱም አልፎ የዓለም ቅርስ በመሆን በዩኔስኮ ተመዝግቦ የሚገኝ እሴት መሆኑ ይታወቃል።

በዓሉ በዛሬው እለት በመላ ኢትዮጵያ ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቱን በተጠበቀ መልኩ ተከብሯል።

በትግራይ ክልልም በደማቅ ስነስርአት መከበሩን በተለያዩ አካባቢዎች የተንቀሳቀሱ የኢዜአ ሪፖርተሮች አረጋግጠዋል።

የርዕሰ አድባራት ወገዳማት አክሱም ፂዮን ማርያም አስተዳዳሪ ቆሞስ ንቡረ ዕድ አባ መሀሪ ሀብቴ፤ በተፈጠረው ሰላምና መረጋጋት የዘንድሮው የጥምቀት ክብረ በዓል የቀድሞውን ክብር ጠብቆ በድምቀት ተከብሯል ብለዋል።

አክሱም የጥምቀት መጀመሪያ እና ከጥንትም ጀምሮ ለዘመናት ጥምቀትን በድምቀት ስታከብር መኖሯን አስታውሰው ከነበረው ግጭትና ስጋት በመውጣት ዘንድሮ በደማቅ ሁኔታ መከበሩን ገልጸዋል።

የሰላም ጉዳይ የሁሉም መሰረትና የመኖር ዋስትና መሆኑን የተናገሩት ቆሞስ ንቡረ ዕድ አባ መሀሪ ሀብቴ፤ ለተጀመረው ሰላም ዘላቂነት ሁላችንም የድርሻችንን ልንወጣ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፀሎት ሁልጊዜም ስለ ሰላም፣ ፍቅርና አብሮነት መሆኑን ጠቅሰው ዘላለማዊ ሰላምን ተመኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም