በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ በድምቀት የሚከበረው የጥምቀት በዓል የቱሪዝም መዳረሻ እየሆነ ነው

ደብረ ብርሀን (ኢዜአ) ጥር 10/2015 በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ በየዓመቱ በድምቀት የሚከበረው የጥምቀት በዓል የቱሪዝም መዳረሻ እየሆነ መምጣቱን የወረዳው አስተዳዳር ገለጸ።

በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ የከተራ በዓል በርካታ የእምነቱ ተከታዮችና እንግዶች በተገኙበት በድምቀት እየተከበረ ነው።

በበዓሉ ላይ የተገኙት የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ አይችሉህም ጠናጋሻው ለኢዜአ እንደገለጹት፣ የምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጥምቀት በዓል አማካኝነት የቱሪስት መስህብ እየሆነች መጥታለች።

በወረዳው የራንቡቲ አምሳለ ዮርዳኖሰ የከተራና ጥምቀት በዓል ለቱሪስት መዳረሻ ለመሆን የበቃው በሸንኮራ ወንዝ 44 ታቦታት በአንድ ላይ ወጥተው የሚያድሩበት ታላቅ በዓል በመሆኑ እንደሆነም አስረድተዋል።

ወረዳው ያሉትን ሃይማኖታዊና ባህላዊ የቱሪዝም መዳረሻዎች አልምቶ ከዘርፉ የሚገኝን ገቢ ለማሳደግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብበር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ጥምቀትን የቱሪስት መዳረሻ ማድረጉ የወረዳውን እምቅ የኢንቨስትመንት አቅም በማስተዋወቅ የውጭና የአገር ውስጥ ባለሃብቶች ወደአካባቢው መጥተው እንዲያለሙ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርም አስረድተዋል ።

በአሁኑ ወቅት 44 ታቦታት በበርካታ ምዕመናን ታጅበው በራንቡቲ ቀበሌ የሸንኮራ ወንዝ ጥምቀት ባህር የደረሱ ሲሆን፣ በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ የጸጥታ ሃይሉና ወጣቶች በጋራ እየሰሩ መሆኑንም አቶ አይችሉህም ተናግረዋል።

የባልጭ ደብረሰላም ቅዱስ አማኑኤል ታቦትን አጅበው ሲጓዙ ከነበሩ ምዕመናን መካከል ወይዘሮ በላይነሽ ተሻለ እንደገለጹት፣ የሀገሪቱ ሰላም ተረጋግጦ ጥምቀትን በሰላምና በአብሮነት በማክበራቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።

ሃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላትን በአንድነት ከማክበር ጎን ለጎን በቀጣይ ለዘላቂ ሀገራዊ ሰላም የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጥዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም