የኦሮሚያና የሶማሌ ክልሎች ተፈናቃዮች ''ተገቢ ድጋፍ አልተደረገልንም'' አሉ - ኢዜአ አማርኛ
የኦሮሚያና የሶማሌ ክልሎች ተፈናቃዮች ''ተገቢ ድጋፍ አልተደረገልንም'' አሉ
ደሴ መስከረም 23/2011 ከኦሮሚያና ከሶማሌ ክልሎች ተፈናቅለው በደቡብ ወሎ ዞን አምባሰል ወረዳ የሚገኙ 100 ሰዎች ''ተገቢ ድጋፍ አልተደረገልንም'' አሉ። የአምባሰል ወረዳ አስተዳደር በበኩሉ በወረዳው አቅም ተፈናቃዮቹን ለመርዳት ጥረት ቢያደርግም፤ ጥያቄው ከአቅሙ በላይ በመሆኑ “ለዞኑ አስተዳደር አሳውቀን ምላሽ እየተጠባበቅን ነው” ብሏል። ከተፈናቃዮቹ በኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋ ተወልደው ማደጋቸውን የገለጹት የ36 ዓመቱ አቶ ዋሴ አሰፋ፣ በአካባቢው በተፈጠረው አለመረጋጋት ለዘመናት ያፈሩትን ሃብትና ንብረት ትተው መምጣታቸውን ይናገራሉ፡፡ በግጭቱ ምክንያት ወደ ውጫሌ ከመጡ አንድ ዓመት ገደማ ቢሆናቸውም፤ እስካሁን ወረዳው ያደረገላቸው ድጋፍ ''የቤት ኪራይ እንኳ የማይሸፍን ነው''ብለዋል፡፡ ''የተሻለ ገቢ የነበረን ሰዎች የዕለት ጉርሳችንን ለመሸፈንና ቤተሰባችንን ለመርዳት በጉልበት ሥራ ለመሰማራት ተገድደናል'' የሚሉት አቶ ዋሴ፣ በተደጋጋሚ ድጋፍ እንዲደረግልን ለዞኑ አስተዳደር ጥያቄ ብናቀርብም ምላሽ አላገኘንም ብለዋል፡፡ በሶማሌ ክልል ደገሃቡር ዞን ደገሃመዶ አካባቢ በመምህርነት ያገለግሉ እንደነበርና በተፈጠረው አለመረጋጋት ወደ ውጫሌ ከመጡ ሳምንት እንዳለፋቸው የሚናገሩት ደግሞ መምህር ሰይድ ታደሰ የተባሉ አስተያየት ሰጪ ናቸው፡፡ ከመንግሥትም ሆነ ከግብረ ሰናይ ድርጅቶች የተደረገላቸው ምንም ዓይነት ድጋፍ እንደሌለና ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት “በተደጋጋሚ ጥያቄ ብናቀርብም፤ ለችግራችን ተገቢውን ምላሽ አልሰጠንም” ብለዋል፡፡ ተፈናቃዮቹ በእጃቸው የያዙት ምንም ዓይነት ገንዘብ ባለመኖሩ ለረሃብና ለሌሎች ችግሮች መዳረጋቸውን ነው የተናገሩት፡፡ ከተፈናቃዮቹ ውስጥ ብዙዎቹ አካል ጉዳተኞች፣ አቅመ ደካሞችና፣ ሴቶችና ህጻናት መሆናቸውን ጠቁመው፣ የከፋ ሰብዓዊ ቀውስ ከመከሰቱ በፊት መንግሥት የምግብ፣ የአልባሳትና የመጠለያ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል፡፡ የአምባሰል ወረዳ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ብርሃኔ አያሌው የወረዳው ሴክተር መሥሪያ ቤቶችንና ወርልድ ቪዥን ከተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት በማስተባበር 111 ሺህ ብር ገደማ የሚያወጣ የዕለት ምግብ ድጋፍ ማድረጉን አስረድተዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበርና ከወረዳው አስተዳደር ጽህፈት ቤት የተገኘ 73 ብርድ ልብስ መከፋፈሉን ገልጸዋል። ሆኖም ተፈናቃዮቹ ያሉበትን አሳሳቢ ሁኔታ በመግለጽ አስቸኳይ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ለደቡብ ወሎ ዞን አስተዳደርና ለአማራ ክልል መንግሥት በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርቡም፤ እስካሁን ምላሽ አለማግኘታቸውን ጠቁመዋል፡፡ በደቡብ ወሎ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ቡድን መሪ አቶ መሐመድ ሰይድ እንዳሉት ከኦሮሚያና ከሶማሌ ክልሎች ተፈናቅለው ወደ ዞኑ የሚገቡ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል። ለተፈናቃዮቹ ከወሎ ዩኒቨርሲቲና ከረጂ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የምግብና የአልባሳት ድጋፍ ለመስጠት የሚያደርጉት ጥረት ከችግሩ ውስብስብነት አንጻር በቂ አይደለም ብለዋል። በኮምቦልቻና ኃይቅ ከተሞች ከሰፈሩት ተፈናቃዮች ውስጥ 38 አባዎራዎች ሁለተኛ ዲግሪና ልዩ ሙያ ያላቸው በመሆናቸው ሥራ የሚያገኙበትን ሁኔታ በአካባቢው በባቡር መሥመር ዝርጋታ ላይ ከተሰማራው ያፒ መርከዚ ጋር እየተነጋገሩ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እጅጉ መላኬ በበኩላቸው በዞኑ ሰባት ወረዳዎች 600 የሚጠጉ ተፈናቃዮች መኖራቸውን አመልክተው፣ ወረዳዎቹ ከተመደበላቸው መጠባበቂያ በጀት አምስት በመቶ በመመደብ የዕለት ዕርዳታ እንዲያደርጉ አቅጣጫ ተቀምጦ በመሰራት ላይ ነው ብለዋል። ለተፈናቃዮቹ የመኖሪያ ቤቶች በመገንባት፣ የዕለት ምግብና አልባሳት በማቅረብ በዘላቂነት ለማቋቋም 24 ሚሊዮን ብር ገደማ እንደሚያስፈልግም አስታውቀዋል። ወጪውን በዞኑ አቅም መሸፈን ስለማይቻል ለሚመለከተው መንግሥታዊ አካልና ለአጋር ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ማሳወቃቸውነና በዞን ደረጃ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑን አስረድተዋል።፡ በደቡብ ወሎ ዞን ከኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች የተፈናቀሉ ወገኖች በኮምቦልቻ፣ተሁለደሬ፣ አምባሰል፣ ኩታብር፣ ወረባቦና መቅደላ ወረዳዎች እንደሚገኙ ከአስተዳደሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡