ቀጥታ፡

የጥምቀት በዓል ኃይማኖታዊ ስርዓቱንና ትውፊቱን ጠብቆ በድምቀት እንዲከበር ማድረግ የመላው ኢትዮጵያውያን ኃላፊነት ነው -የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 10/2015 የጥምቀት በዓል ኃይማኖታዊ ስርዓቱንና ትውፊቱን ጠብቆ በድምቀት እንዲከበር ማድረግ የመላው ኢትዮጵያውያን ኃላፊነት ነው ሲል የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገለጸ።

ምክር ቤቱ የጥምቀት በዓልን በማስመልከት ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል።

በመልዕክቱም በዓሉ ኃይማኖታዊ ስርዓቱንና ትውፊቱን ጠብቆ በድምቀት እንዲከበር ማድረግ ለእምነቱ ተከታዮቹ ብቻ የሚተው ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያውያን ኃላፊነት ነው ብሏል።

የጥምቀት በዓል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን በአደባባይ ከምታከብራቸው ዐበይት በዓላት መካከል አንዱ መሆኑን ምክር ቤቱ ገልፆ በዓሉ የሰላም፣ የፍቅር፣ የዕርቅና የመተሳሰብ በዓል ሆኖ እንዲያልፍ መልካም ምኞቱን ገልጿል።

በዓሉ ከኃይማኖታዊ አስተምህሮና እሴቱ ባለፈ የኢትዮጵያውያንን ማህበራዊ ትስስር የሚያጠናክር፣ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴን የሚያሳልጥ እና ለሀገር ገፅታ ግንባታና ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው ዕድገት ያለው ጠቀሜታ እጅግ ከፍተኛ ነው ሲልም አስታውቋል።

በዓሉ ያለምንም የፀጥታ ችግር ተከብሮ እንዲጠናቀቅ ለማድረግ በተረጋጋና በሰከነ መንፈስ በመንቀሳቀስ ህብረተሰቡ ሰላሙን እንዲጠብቅም ምክር ቤቱ ጥሪውን አስተላልፏል።

ምክር ቤቱ በመልዕከቱ የሚመለከታቸው የመንግሥት የጸጥታ አካላትም ኃላፊነታቸውን በትጋትና ኃላፊነት በተሞላበት ስሜት እንዲወጡም ምክር ቤቱ አሳስቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም