የጥምቀትን በዓል ስናከብር የቆየውን የመደጋገፍ እሴታችንን በሚያጠናክር መልኩ ሊሆን ይገባል -ርዕሰ መስተዳደር ርስቱ ይርዳው - ኢዜአ አማርኛ
የጥምቀትን በዓል ስናከብር የቆየውን የመደጋገፍ እሴታችንን በሚያጠናክር መልኩ ሊሆን ይገባል -ርዕሰ መስተዳደር ርስቱ ይርዳው
ሀዋሳ (ኢዜአ) ጥር 10 / 2015 የጥምቀት በዓልን ስናከብር የቆየውን የመረዳዳትና የመደጋገፍ እሴታችንን በሚያጠናክር መልኩ ሊሆን ይገባል ሲሉ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳው መልዕክት አስተላለፉ።
ርዕሰ መስተዳደሩ በዓሉን በማስመልከት ዛሬ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ኢትዮጵያዊያን የተቸገሩ ወገኖቻችንን የመደገፍና የመርዳት የቆየ ልምድ ያለን ህዝቦች ነን ሲሉ ገልጸዋል።
የጥምቀት በዓል ሲከብርም ያለውን የቆየ የመተጋገዝ ልምድ የበለጠ በማጠናከር የተቸገሩ ወገኖችን በማገዝ ጭምር መሆን እንዳለበት አመልክተዋል።
በዓለም የማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገበው ጥምቀት የአለም ህዝቦች በዓል መሆኑን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በዓሉን ስናከብር እሴቶቻችንን በሚያጠናክር መልኩ ሊሆን ይገባል ብለዋል።
"የጥምቀት በዓል የሀገሪቱን መልካም ገጽታ በመገንባት ረገድ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ሀገራችንን ከፍ የሚያደርጉ ተግባራትን ልናስተዋውቅበት ይገባል" ሲሉም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በየጊዜው የሚያጋጥሟትን ፈተናዎች በዜጎቿ ጥረት እየተሻገረች ለዚህ በቅታለች ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ፤ አሁን የተገኘውን ሰላም በዘላቂነት በማስቀጠል በተሰማራንበት መስክ ጠንክረን መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።
ዘንድሮ የሚከበረው በዓል ሀገሪቱ በሁሉም መስክ በርካታ ድሎችን ባስመዘገበችበት ጊዜ ላይ መሆኑ የተለየ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።
ለመላው የክልሉና የኢትዮጵያ ህዝብ በዓሉ የሰላም፣ የጤና፣ የፍቅር፣ የአንድነትና የመረዳዳት በዓል እንዲሆንም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።