ቀጥታ፡

የጥምቀት በዓል በሰላም እንዲከበር የጸጥታ አካላት በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ

አዲስ አበባ (ኢዜአ)ጥር 10/2015 የከተራና የጥምቀት በዓል በሰላም እንዲከበር የጸጥታ አካላት በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።

 በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረውን ችግር በሰላማዊ ውይይት በመፍታት ዘላቂ ሰላም ለማስፈን መንግሥት እያደረገ ያለውን ጥረት አጠናክሮ መቀጠሉንም ገልጿል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ፤ የጥምቀት በዓል አከባበር ዝግጅት፣ አገራዊ የሰላም እና ደኅንነት ጉዳዮችን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም የከተራና ጥምቀት በዓል ሰላማዊነት ለማስጠበቅ የጸጥታ ኃይሉ የተሟላና በቂ ዝግጁት ማድረጉን ተናግረዋል።

ከተለያዩ ዓለማት የሚመጡ ቱሪስቶችን በተገቢው መንገድ ተቀብሎ በማስተናገድ ሕብረተሰቡ የተለመደ እንግዳ ተቀባይነቱን እንዲያሳይ ጠይቀዋል።

ከማይዳሰሱ የዓለም ሕዝቦች ወካይ ቅርስ ሆኖ የተመዘገበው የጥምቀት በዓል በሰላም እንዲከበር የፌደራል እና የክልል የጸጥታ አካላት በቂ ዝግጅት አድርገዋል ሲሉ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

የሰሜኑን ችግር በሰላም ለመቋጨት መንግሥት የጀመራቸውን ዘርፈ-ብዙ ጥረቶች አጠናክሮ መቀጠሉን አረጋግጠው የሰብአዊ ድጋፍ ተደራሽነትም በስፋት በመከናወን ላይ ነው ብለዋል።

በአፋር፣ አማራና ትግራይ ክልሎች በጦርነት ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ከዓለም አቀፍ ረጂ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ሰብዓዊና ቁሳዊ ድጋፍ እየቀረበ መሆኑንም ገልጸዋል።

በትግራይ ክልል የጤና፣ ትራንስፖርት፣ ባንክ፣ ቴሌኮም፣ መብራትና ሌሎችም አገልግሎቶች ሥራ እንዲጀምሩ መደረጉን ተናግረዋል።

በፕሪቶሪያ የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ የህወሓትን ታጣቂዎች ወደ ካምፕ የማስገባት እና የነበራቸውን   ከባድ መሳሪያ የመረከብ ሥራ መጀመሩን አስታውሰዋል።

የትግራይ ክልልን የንግድ እንቅስቃሴ በማስፋት የኑሮ ውድነት እንዲረጋጋ እና አምራች ኢንዱስትሪዎችም ወደ ሥራ እንዲገቡ ለማድረግ በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሰውን የሸኔ ሽብር ኃይል እያስከተለ የሚገኘውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስጋት ለመግታትም መንግሥት ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የተቀናጀ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የሽብር ቡድኑ የሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲመለሱ የመንግሥትና የክልሉ የጸጥታ ኃይል ሕዝብን ያሳተፈ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑንም ተናግረዋል።

የሽብር ቡድኑ ከጥፋት ኃይሎች ጋር ጥምረት በመፍጠር ሕገ-ወጥ ታጣቂዎችን አደራጅቶ በንጹሃን ዜጎች ህይወት፣ ሃብትና ንብረት ላይ የደቀነውን አደጋ ለመቀልበስም የተቀናጀ እርምጃ እየተወሰደ ነው ብለዋል።

መንግሥት ማንኛውንም ችግር በሰላማዊ መንገድ መፍታት የሚል ጽኑ አቋም በመያዝ እየሰራ መሆኑንም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም