የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የዘመናዊ አዳዲስ ትጥቆች ባለቤት ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የዘመናዊ አዳዲስ ትጥቆች ባለቤት ሆነ
አዲስ አበባ ጥር 10/2015 /ኢዜአ/ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የዘመናዊ አዳዲስ ትጥቆች ባለቤት ሆነ ።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የዘመናዊ አዳዲስ ትጥቆች ባለቤት መሆኑ ይፋ የተደረገው የኮማንዶ እና የአድማ ብተና ኃይሎች በአዲስ አበባ ከተማና ዙሪያው የተግባር ልምምድ በአደረጉበት ወቅት ነው።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በስራ ላይ ያሰለጠናቸውን ኮማንዶ እና አድማ ብተና የደረሱበት ብቃት እና የትጥቅ አቅሞች በኮሚሽነር ጀነራል እና በማኔጅመንት አባላት ተጎብኝቷል።
በጉብኝቱም አዳዲስ የገቡ የትጥቅ አቅሞች፣ የኮማንዶ እና የአድማ ብተና ኃይል ሲያካሄዱ የነበረውን ሥልጠና በተግባር ለከፍተኛ አመራሮቹ አሳይተዋል።
የኮማንዶ እና የአድማ ብተና ኃይል በተግባር ባሳዩት ብቃት ከፍተኛ አመራሮቹ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
ፖሊስ ለመጀመሪያ ጊዜ BRMD 2 የተባለ ራሺያ ሰራሽ ባለ ጎማ ታንክ በመንግስት እና በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም እገዛ የትጥቅ ባለቤት ሆኗል።
ለተደረገው ድጋፍም ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል አድናቆትና ምስጋናቸውን ገልጸዋል።
ኮሚሽነር ጀነራሉ ለድጋፉ አስተዋጽኦ ላደረጉት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እና ለመከላከያ ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን የላቀ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ተንቀሳቃሽና ቋሚ የደህንነት ካሜራዎችን ጭምር በመጠቀም ለአገርና ለህዝብ ሰላምና ደህንነት አስፈላጊውን ሁሉ ጥበቃ እያደረገ መሆኑ ይታወቃል።