በልማት ወደ ኋላ የቀሩ አገራት፣ የባህር በር የሌላቸው ታዳጊ አገራት እና ትናንሽ ደሴቶች የደቡብ ደቡብ ትብብርን በማጠናከር የድህነት ቅነሳ እና የዘላቂ ልማት ግቦቻቸውን ለማሳካት መንቀሳቀስ አለባቸው-አቶ ደመቀ መኮንን

25

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 10/2015፦ በልማት ወደ ኋላ የቀሩ አገራት፣ የባህር በር የሌላቸው ታዳጊ አገራት እና ትናንሽ ደሴቶች የደቡብ ደቡብ ትብብርን በማጠናከር የድህነት ቅነሳ ግቦቻቸውን ለማሳካት መስራት እንዳለባቸው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ተናገሩ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከፍተኛ ተወካይ እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ረዳት ዋና ፀሐፊ አምባሳደር ራባብ ፋጢማን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

በውይይታቸውም በልማት ወደ ኋላ የቀሩ አገራት፣ የባህር በር የሌላቸው ታዳጊ አገራት እና ትናንሽ ደሴቶች የደቡብ ደቡብ ትብብርን በማጠናከር የድህነት ቅነሳ ግቦቻቸውን ለማሳካት መስራት እንዳለባቸው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገልጸዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም ሀገራቱ የዘላቂ ልማት ግቦቻቸውን ለማሳካትም መንቀሳቀስ አለባቸው ብለዋል።

አቶ ደመቀ እነዚህ አገራት በተለያዩ መድረኮች በሚኖራቸው ተሳትፎ በልማት የበለፀጉ አገራት የፋይናንስ ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው የጋራ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ማድረግ አለብን ብለዋል።

ይህን መሰል ተግባራት በተቀናጀ መንገድ ለማስኬድ ዶሃ ፎረም ወሳኝ ሚና እንደሚወጣም ገልፀዋል።

አምባሳደር ራባብ ፋጢማ በበኩላቸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በልማት ወደ ኋላ የቀሩ አገራት፣ የባህር በር የሌላቸው ታዳጊ አገራት እና ትናንሽ ደሴቶች ከድህነት ወጥተው ወደ ተሻለ የእድገት ሽግግር እንዲያደርጉ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

ኢትዮጵያም የዚህ ቡድን አባል አገር እንደ መሆኗ የበኩሏን ሚና እንድትጫወት አምባሳደሯ ጥሪ ማቅረባቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል-አቀባይ ጽህፈት ቤት መረጃ ያመላከታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም