ሕዝበ ክርስቲያኑ የጥምቀት በዓልን ሲያከብር እርስ በእርስ በመረዳዳትና በመተጋገዝ ሊሆን ይገባል

ጥር 9/2015 /ኢዜአ/ "ሕዝበ ክርስቲያኑ የጥምቀት በዓልን ሲያከብር እርስ በእርስ በመረዳዳት ሊሆን ይገባል" ሲሉ የሃይማኖት መምህሩ ዲያቆን ቴዎድሮስ በለጠ ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በየዓመቱ ከምታከብራቸው ዘጠኝ ዓበይት በዓላት መካከል ጥምቀት አንዱ ነው።

ጥምቀት ከዋዜማው "ከተራ" እስከ ሦስተኛው ቀን "ቃና ዘገሊላ" በተከታታይ በአደባባይ በከፍተኛ ድምቀት ይከበራል።

ይህ ታላቅ ሃይማኖታዊ በዓል ከሃይማኖታዊ በዓልነቱ ባሻገር ባህላዊ ፋይዳው የጎላ እንደሆነ ይታመንበታል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የሃይማኖት መምህርና ሰባኪ የሆኑት ዲያቆን ቴዎድሮስ በለጠ የጥምቀት በዓል " የሰላም በዓል ነው" ይሉታል።

በዓሉ ሰዎች እርስ በእርስ በአብሮነት የሚያሳልፉት ከሁሉ በላይ ደግሞ ትህትናን የምንማርበት ትልቅ ሃይማኖታዊ በዓል መሆኑን ነው ያሰመሩበት።

በመሆኑም የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊ ሥርዓቱንና ትውፊቱን ሳይለቅ በሰላም እንዲከበር የማድረግ ትልቅ ኃላፊነት አለብን ሲሉ ተናግረዋል።

በተለይም የእምነቱ ተከታይ ወጣቶች የሃይማኖት አባቶች የሚሰጡትን ትምህርት በመከተል በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል ነው ያሉት የሃይማኖት መምህሩ ዲያቆን ቴዎድሮስ።

ሕዝበ ክርስቲያኑ የጥምቀት በዓል ትልቅ ሃይማኖታዊ ትርጉም ያለው መሆኑን በመገንዘብ በዓሉን ሲያከብር ሃይማኖታዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ መሆን እንዳለበት ገልጸዋል።

በተለይም ደግሞ እርስ በእርስ በመረዳዳትና በመተጋገዝ ሊሆን እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የጥምቀት በዓል በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2019 ነበር በማይዳሰስ የባህል ቅርስነት የተመዘገበው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም