የአብሮነት እሴቶቻችንን ለዓለም የምናሳይበት የጥምቀት በዓል

119

የጥምቀት በዓል በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ሳይንስና ባህል ድርጅት(ዩኔስኮ) በዓለም የማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገበ ሲሆን፤ በዚህም የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ቀልብ እየሳበ የመጣ ታላቅ ሃይማኖታዊ ክብረ በዓል ነው።

ይህም ከሃይማኖታዊ በዓልነቱ ባሻገር ባህላዊ እና ስነ-ልቦናዊ ፋይዳው የጎላ ያደርገዋል፡፡

የጥምቀት በዓል ኢትዮጵያዊያን የኃይማኖት መቻቻል እና ነጻነትን እንዲሁም አብሮነትን ለዓለም የሚያሳዩበት የሰላም መገለጫ መሆኑም ይወሳል፡፡

በዚህም በርካታ የውጭ አገር ጎብኚዎች ፣በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና መንፈሳዊ ተጓዦች በበዓሉ ላይ ይታደማሉ፡፡

ኢዜአ ያነጋገራቸው የስነ-ልቦና ባለሙያ አቶ ሲሳይ ቱፋ፤የጥምቀት በዓል ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እሴቶቻችንን የምናሳይበት እና በርካታ ስነ-ልቦናዊ ጥቅሞች የሚገኙበት ነው ሲሉ ይገልጻሉ፡፡

በገጠሩ የኢትዮጵያ ክፍል የጥምቀት በዓል ወጣቶች የሚተጫጩበትና የትዳር አጋር የሚመርጡበት ዋነኛ እለት ነው ብለዋል፡፡

በበዓሉ ዐለት የሚከናወነው የሎሚ ውርወራና በወጣቶች የሚቀነቀኑት ሕብረ-ዝማሬዎች አንድነትን የሚያጠናክሩ መሆናቸውን አቶ ሲሳይ ያመለከቱት፡፡

ይህም በዓሉ ኢትዮጵያዊያን ለዘመናት ያስተሳሰራቸውን የማህበረሰብ መስተጋብር እንደሚያሳይ የጠቀሱት የስነ ልቦና ባለሙያው በዓሉም አንድነትና አብሮነትን በተግባር እንደሚያሳይ ገልጸዋል፡፡

የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ እምነትና ቀኖና መሰረት ከዘጠኙ ዐቢይ በዓላት አንዱ ነው፡፡

በዓሉም ከዋዜማው (ከተራ) ጀምሮ ታቦታቱ ከየአብያተ ክርስቲያናቱ በክብር ወጥተው በሕዝቡ እልልታ፣ ሽብሽባ እና በካህናቱ ውብ ያሬዳዊ ዜማ ወደ ወንዝ አልያም ወደ ተዘጋጀ የውኃ ቦታ በመውረድ ይከበራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም