በትግራይ ክልል የጥምቀት በዓል በሰላም እንዲከበር አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል- ፌደራል ፖሊስ - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ ክልል የጥምቀት በዓል በሰላም እንዲከበር አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል- ፌደራል ፖሊስ
ጥር 09 ቀን 2015 (ኢዜአ) በትግራይ ክልል የጥምቀት በዓል በሰላም እንዲከበር አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ገለፀ።
በፌደራል ፖሊስ የትግራይ ክልል አስተባባሪ ምክትል ኮሚሽነር ሐብታሙ ካሳ፤ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ለበዓሉ ሰላማዊ ክንውን በፖሊስ በኩል በበቂ ዝግጅት ስምሪት መደረጉን ገልጸዋል።
ከአደባባይ በዓላት መካከል አንዱ የሆነው የጥምቀት በዓል በሰላም እንዲከበር ለማድረግ ሕብረተሰቡ ከጸጥታ ኃይሉ ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ከሰላም ስምምነቱ በኋላ የአክሱም ጽዮን እና ሽሬ ላይ የጥር ሥላሴ ንግስ በዓላት በሰላም መከበሩን አስታውሰው፤ ለሰላምና የጸጥታ ሥራ ሕብረተሰቡ ጠንካራ ትብብር እንዳደረገ ገልጸዋል።
የከተራና የጥምቀት በዓላትም በተመሳሳይ መልኩ እንደሚከበሩ ጠቅሰው፤ ለዚህም ፌደራል ፖሊስና ሕብረተሰቡ በትብብር እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የሽሬ ከተማ ነዋሪዎችም የጥምቀት በዓልን በድምቀት ለማክበር መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
የጥምቀት በዓል ከሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ባሻገር የሕዝቦችን አንድነት የሚያጸና፣ ሕዝባዊ ትስስርን የሚያጠናክር በዓል መሆኑ ይታወቃል።