ቀጥታ፡

አመራሮች ዝርፊያና የመጠላለፍ ፖለቲካን በማስቀረት ለአገሪቱ አንድነትና እድገት ሊሰሩ ይገባል-ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ

አዲስ አበባ መስከረም 23/2011 አመራሮች ዝርፊያና የመጠላለፍ ፖለቲካን በማስቀረት ለአገሪቱ አንድነትና እድገት እንዲሰሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጥሪ አቀረቡ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሄን ያሉት በሀዋሳ በመካሄድ ላይ ባለው 11ኛው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ድርጅታዊ ጉባኤ ላይ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ነው። ቀደም ሲል ለጊዜያዊ ጥቅምና ግላዊ ክብር ሲሉ አገሪቱን ለጠላቶቿ አሳልፈው ሰጥተው "መዘባበቻ ያደረጓት መሪዎች" እንደነበሩ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዜጎች መካከል የመከፋፈል፣የመለያየትና የአለመተማመን ሁኔታዎችን የፈጠሩ አምባገነን መሪዎች እንደነበሩም እንዲሁ። ይሁን እንጂ በጠብና በጦርነት ሊጠፋፉ የዘመቱ ልጆቿን አስታርቀው አንድ ያደረጉ መሪዎችም ያላት አገር መሆኗን የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አሁን ያሉ መሪዎችም ይሄንኑ አርዓያ በመከተል እንዲሰሩ አስገንዝበዋል። አሁን በአገሪቱ እየታየ ያለውን የለውጥና የተስፋ ጭላንጭል በማጥፋት ለጠላቶቿ መፈንጫ ለማድረግ የሚታትሩ ኃይሎች ከድርጊታቸው ተቆጥበው አገሪቷን ዓለም ከደረሰበት የስልጣኔ ማማ ለማድረስ አጥብቀው እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ "እኛ የዛሬዎቹ መሪዎች ይህችን ታሪካዊ አገር ልትሰምጥ ነው ከተባለችበት አዘቅት ውስጥ አውጥተን የልጆቿ ክብርና ኩራት እናደርጋታለን ወይስ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ውስጥ መሆናችንን ዘንግተን እርስ በእርሳችን በእርስትና ጉልት እየተፋጀን የልጆቻችን ማፈሪያና የዓለም መሳቂያ እናደርጋታለን'?" ሲሉም የጉባኤው ታዳሚያንን ጠይቀዋል። አገሪቱ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ብልጽግና ዘላቂ ሀብቷ አድርጋ የጨበጠች ዘመናዊና ስልጡን ኢትዮጵያን ለመፍጠር ቅድሚያ "ህዝቡን የሉዓላዊ የስልጣን ምንጭ አድርጎ መቀበል ግድ ነው" ብለዋል። ኃላፊነቱን በነጻ ምርጫ እንዲወሰን በማድረግና በህዝብ ውሳኔ የሚገዛ አመራር መኖርም አስፈላጊ ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ። በተጨማሪም አመራሩ ህዝቡን በዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ማሳተፍና ማካተትን መናበብና መደማመጥን ድልብ የማህበራዊ ኃብትን የመጠቀም የአመራር ዘዬን የመጠቀም ልምድ ማካበት ይኖርበታልም ብለዋል። በዚህም ስኬታማነት የሚረጋገጠው ህዝብ የሚያዳምጣቸውና የሚከተላቸው የሃይማኖት አባቶች፣የአገር ሽማግሌዎች፣የሞራልና የግብረ ገብ መሪዎች፣የእውቀትና የሊህቃን ምሁራን በማፍራት ነው። በተጨማሪም በስራና ሃብት ፈጠራ የተካኑ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪና የብልጽግና ቁመና ያላቸው ማህበራዊ ሃላፊነታቸውን የሚወጡ የሃብት አንቀሳቃሾች ፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ምርምርና ጥናት አገርን ዓለም ከደረሰበት እድገት ላይ በፈጣን ግስጋሴ የሚያደርሱ ዜጎችን ተሳትፎ በማጎልበት ነው ብለዋል። እንዲሁም ተመራማሪዎችና መምህራን በየዘርፉ በብዛት ከተገኙ፣ ግጭትና ሽብር በበዛበት ዓለም ውስጥ የሉዓላዊነታችን መከበር ለሰላማችን መረጋገጥ በሰለጠነ መንገድ አገርን የሚጠብቁ ስልጡን የጦር መሪዎች ሊኖሩን ይገባልም ብለዋል። በሙያዊ ክህሎታቸውና አመለካከታቸው የበሰሉ የአገልጋይነት መንፈስ የተላበሱ አመራሮች ህግና ደንብ በማስከበር በህክምና፣በምህንድስና ፣ በኮንስትራክሽን፣ በግብርና በሌሎች የስራ መስኮች የተሰማሩ በሚዲያ፣ በጥናትና ምርምር ተቋማት፣ በሲቪክ ማህበራትና በሌሎች የዴሞክራሲ ተቋማት ያሉ ዜጎች በሃላፊነት በመስራት ህዝብን የማንቃት ሚናቸውን በስፋት ሊወጡ ይገባል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ። ፖለቲከኞች ሃሳባቸውን በነጻነት የሚያንሸራሽሩባት አገር ለመፍጠርና ብዝሃነትን ጥቅም ላይ እንዲውል በጋራ ለመስራት የአመራሩ ቁርጠኛ መሆንን ይጠይቃል። ዝርፊያና የመጠላለፍ ፖለቲካን በማስቀረት ለአገር እድገት ለመስራት ህዝቦቿን ጨምሮ አመራሩ ሃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባም ጠቁመዋል። እኩልነትና ነጻነት የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለመፍጠርም ከዘርና ከሃይማኖት ልዩነት በመውጣት ለሌሎች አብሮነት መስራት ያስፈልጋልም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም