በጋምቤላ ክልል ብልሹ አሰራሮች የወለዷቸውን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት በትኩረት ይሰራል - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ክልል ብልሹ አሰራሮች የወለዷቸውን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት በትኩረት ይሰራል
ጋምቤላ (ኢዜአ) ጥር 9/2015 በጋምቤላ ክልል ሌብነትና ብልሹ አሰራሮች የወለዷቸውን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት በትኩረት እንደሚሰራ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ አስታወቁ።
የመልካም አስተዳደር ቅሬታዎችና አቤቱታዎች መፍታት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ የክልል፣ የዞንና የወረዳ አመራሮች ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ተወያይተዋል።
በወቅቱ ርዕሰ-መስተዳደር ኢሞድ ኡጁሉ፤ በክልሉ ሌብነትና ብልሹ አሰራሮች የወለዷችው በርካታ የመልካም አስተዳደር ቅሬታዎችና አቤቱታዎች እየቀረቡ ናቸው ብለዋል።
በክልሉ በተለይም ከመሬት አስተዳደር፣ ከፍትህና ሌሎች አገልግሎቶች ጋር በተያያዘ ከህዝቡ ቅሬታዎች እየቀረቡ መሆኑን ተናግረዋል።
ለክልል የቀረቡትን ሳይጨምር ባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታ ከክልሉ 34 ያህል የመልካም አስተዳደር ቅሬታዎችና አቤቱታዎች ለፌዴራል መንግስት መቅረባቸውን ጠቅሰዋል።
የመልካም አስተዳደር እጦት የአንድ አስተዳደር ደካማነት መገለጫ መሆኑን በመገንዘብ በየደረጃው የሚገኙ የአመራር አካላት ችግሩን መፍታት በቁርጠኝነት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።
በተለይም የሌብነትንና የህግ ማስከበር ሂደቶችንና አሰራሮችን አንዳንድ አመራር በውል ያልተገነዘቡበት ሁኔታ መኖሩን ጠቁመው፤ በሰው ኃይል ቅጥርና ሌሎች አገልግሎት አሰጣጦች ላይ በአብዛኛው ቢሮዎች ችግሮች እንዳሉን ገልጸዋል።
በአካባቢው መፈታት የሚችሉ የመልካም አስተዳደርና የአገልግሎት ቅሬታዎችን እልባት በማስይሰጥ አመራር ላይ አዲስ በተቋቋሙ የፀረ-ሙስና ህግ አስከባሪዎች ጭምር እርምጃ የሚወሰድ ይሆናል ብለዋል።
የዕለቱ የውይይት መድረክም ዓላማም አመራሩ በሚነሱ ቅሬታዎች ዙሪያ የጠራ ግንዛቤ በመያዝ ወደ ስራ እንዲገባ ለማስቻል መሆኑን ርዕሰ መስተዳደሩ አስረድተዋል።
ከውይይቱ ተሳተፊዎች መካከል የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ኡቻላ ኡጁሉ በሰጡት አስተያየት፤ በተለይም ከመሬት አስተዳደር ጋር በተያያዘ ለፍርድ ቤቱ በርካታ አቤቱታዎች እየቀረቡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በክልሉ እየተነሱ ያሉትን የመልካም አስተዳደር ቅሬታዎች ለመፍታት የባለድርሻ አካላትን ተቀናጅቶ መስራት የሚጠይቅ ነው ብለዋል።
በወረዳ፣ በዞንና በክልል ደረጃ የሚፈቱ አንዳንድ ቅሬታዎች ወደ ፌዴራል መንግስት የሚሄዱበት አጋጣሚዎች መኖራቸውን ያመለከቱት ደግሞ ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ የማጃንግ ዞን አስተዳደሪ አቶ አብረሃም ማይክል ናቸው።
ተገቢ ባልሆነ ምክንያት ወደ ፌዴራል የሚሄዱ ቅሬታዎች በየአስተዳደር እርከኑ ለመፍታት በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።