ቀጥታ፡

ኢትዮ-ቴሌኮም በሽሬ የሽያጭ ማዕከል በቀን እስከ 700 ደንበኞችን እያስተናገደ ነው

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 9/2015 የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ የኢትዮ-ቴሌኮም ሽሬ ሽያጭ ማዕከል በቀን እስከ 700 ደንበኞችን እያስተናገደ ነው።

የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ ዳግም አገልግሎት ማግኘት የቻለችው ሽሬ ከተማ ነዋሪዎችም የተለያዩ የቴሌኮም አገልግሎቶች ለማግኘት ተሰልፈው ወረፋቸውን ሲጠባበቁ ይስተዋላሉ።

በጦርነቱ ሳቢያ ተፈናቅለው ሽሬ ከተማ ተጠልለው መቆየታቸውን የሚናገሩት ወይዘሮ ፅጌ መስፍን አገልግሎት ለማግኘት ከተሰለፉት መካከል ናቸው።

ከሰላም ስምምነቱ በኋላ በአካባቢው የስልክ አገልግሎት ዳግም ሥራ በመጀመሩ በርካታ ቤተሰቦች ዳግም ለመገናኘት በቅተዋል ይላሉ።

በቅርቡ በአካባቢው የስልክ ኔትዎርክ በመለቀቁ፣ በአቅራቢያቸው ከሚገኘው የኢትዮ-ቴሌኮም ሽያጭ ማዕከል ሲም ካርድ ሲገዙ ያገኘናቸው ወይዘሮ ጽጌ፤ የሰላም ስምምነቱ በእጅጉ ጠቅሞናል ይላሉ።

በተመሳሳይ ወይዘሮ ንግስት ካህሳይ የቴሌኮም አገልግሎት በመጀመሩ ቤተሰቦቻቸውን ማግኘት በመቻላቸው መደስታቸውን ገልጸዋል።

በሽሬ ከተማ የኢትዮ-ቴሌኮም ሽያጭ ማዕከል አስተባባሪ አንዶም በላይ ማዕከሉ ከሁለት ሳምንታት በፊት ሥራ መጀመሩን አስታውሰው፤ የአካባቢው ሕዝብ የቴሌኮም ፍላጎትና አገልግሎት ግን ተመጣጣኝ እንዳልሆነ ገልጸዋል።

ማዕከሉ አንድ ብቻ መሆኑን ጠቅሰው ከአገልግሎቱ አሰጣጥ አኳያ አሁን ላይ በቀን እስከ 700 ደንበኞችን እያስተናገደ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ማዕከሉ የሰው ኃይል አቅሙን በማጠናከር ሌሎች የቴሌኮም አገልግሎቶችን ሲጀምር ችግሩ እንደሚቃለል እምነታቸውን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል የሽሬ ከተማ አጠቃላይ እንቅስቃሴ ወደ ቀደመ ሁኔታው እየተመለሰ መሆኑን ነዋሪዎች ይገልጻሉ።

መምህር ወልዱ ገብሩ የሰላም ስምምነቱ ለሕዝቡ የሰላም ተስፋ የፈነጠቀ ድባብ መፍጠሩን ተናግረዋል።

ከተማዋ ወደ ቀድሞ ሰላማዊ እንቅስቃሴዋ እየተመለሰችና የመሰረተ-ልማት አገልግሎትም እያገኘች መሆኑን ጠቁመዋል።

የተገኘውን ሰላም አስጠብቀን ለመሄድ ሁላችንም የበኩላችንን ልንወጣ ይገባል ብለዋል ነዋሪዎቹ።

የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት በተሟላ ሁኔታ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ በትኩረት መሰራት እንዳለበት ነው አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም