ኢትዮጵያ ምስራቅ አፍሪካን ለማረጋጋትና ቀጠናዊ ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለመፍጠር አስተዋጽኦ ያላት ሀገር ናት-የአውሮፓ ህብረት

139

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 9/2015 ኢትዮጵያ ምስራቅ አፍሪካን ለማረጋጋትና ቀጠናዊ ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለመፍጠር አስተዋጽኦ ያላት ሀገር ናት ሲሉ በአውሮፓ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ተወካይ ዶክተር አኔት ዌበር ገለጹ።

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው በአውሮፓ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ተወካይ ዶክተር አኔት ዌበር ከተመራው የልኡካን ቡድን ጋር በኢትዮጵያና በአውሮፓ ህብረት መካካል ስለሚኖረው ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ትብብር ተወያይተዋል።

በውይይቱም ሚኒስትር ድኤታ ሰመሬታ ሰዋሰው የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ ዘላቂ የልማት አጋር መሆኑን ጠቅሰው ከሰላም ስምምነቱ በኋላ በሰሜን ኢትዮጵያ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለማቋቋም እየተከናወኑ ስላሉ ተግባራት ገለጻ አድርገዋል።

በተጨማሪም ሁለተኛውን የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራዊ በማድረግ የሀገሪቱን ልማትና እድገት ለማፋጠን እየተደረጉ ስላሉ ጥረቶች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

የተጎዱ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለማቋቋምና መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት እንደ አውሮፓ ህብረት ያሉ የልማት አጋሮች የሚያበረክቱትን የሰብዓዊ እርዳታና የልማት ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

የአውሮፓ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ተወካይ ዶክተር አኔት ዌበር በበኩላቸው ኢትዮጵያ ምስራቅ አፍሪካን ለማረጋጋትና ቀጠናዊ ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለመፍጠር አስተዋጽኦ ያላት ሀገር ናት ብለዋል።

በኢትዮጵያ ሰላም መስፈኑ ከአውሮፓ ህብረት ጋር ያለውን ሁለንተናዊ ትብብር ለማጠናከር በጣም አስፈላጊ መሆኑንም አክለዋል፡፡

የአውሮፓ ህብረት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ዘርፈ ብዙ ትብብር ለማጠናከር በቀጣይ ድጋፍ ለማድረግ በህብረቱ በኩል ቁርጠኝነት እንዳለ ማረጋገጣቸውን ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም