ኢህአዴግ በአገሪቱ የህግ የበላይነትን በማስከበር ለውጡን ወደፊት የሚያስቀጥሉ ውሳኔዎች እንዲያስተላልፍ አጋር ድርጅቶች አሳሰቡ - ኢዜአ አማርኛ
ኢህአዴግ በአገሪቱ የህግ የበላይነትን በማስከበር ለውጡን ወደፊት የሚያስቀጥሉ ውሳኔዎች እንዲያስተላልፍ አጋር ድርጅቶች አሳሰቡ
አዲስ አበባ መስከረም 23/2011 ኢህአዴግ በአገሪቱ የህግ የበላይነትን በማስከበር ለውጡን ወደፊት የሚያስቀጥሉ ውሳኔዎች እንዲያስተላልፍ አጋር ድርጅቶች አሳሰቡ። በሀዋሳ እየተካሄደ ባለው 11ኛው የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባኤ ላይ የኢህአዴግ አጋር ድርጅቶች የድጋፍ አቋሞቻቸውን አቅርበዋል። የቤጉህዴፓ ተወካይ አቶ አሻሌ ሀሰን ባደረጉት ንግግር በኢህአዴግ የተደረገው ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ለአጋር ድርጅቶችም በምሳሌነት የሚጠቀስ መሆኑን ተናግረዋል። በኢህአዴግ መሪነት ባለፉት 27 ዓመታት በርካታ የልማት ስኬቶች ቢመዘገቡም አሁንም ያልተመለሱ የህዝቦች የተጠቃሚነትና መብት ጥያቄዎች የቤት ሥራዎቻችን ናቸውም ብለዋል። የህዝቡ መብትና መሰረታዊ ጥቅሞችን ለማስጠበቅና የህግ የበላይነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ውሳኔዎች ከጉባኤው እንደሚጠበቅም ተናግሯል። "መንግስት የሚያሳየው ከመጠን በላይ ያለፈ ትዕግስት" ተገቢ አይደለም ያሉት አቶ አሻሌ ለውጡ እንዳይደናቀፍ ለሚፈጠሩ ክፍተቶች ዕድል መስጠት የለብንም ብለዋል። የአብዴፓ ተወካይ አምበሳደር ሀሰን አብደልቃድር በበኩላቸው ኢህአዴግ በአገሪቱ የፌዴራል ስርዓት በመመስረት በሁሉም መስኮች የሚበረታቱ ለውጦችን ያመጠ ድርጅት መሆኑን እውቅና ሰጥተዋል። ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንዳንድ የአገሪቱ ክፍሎች በሚያጋጥሙ ችግሮች የዜጎች ተዘዋውሮ የመስራትና የመኖር መብት እየተጣሰ በመሆኑ ይሄን የሚፈታ ውሳኔ ከጉባኤው ይጠበቃል ሲሉ ተናግሯል። የህግ የበላይነት እንዲከበር አብረን እንሰራለን ያሉት አምበሳደር ሀሰን፤ በጉባኤው ለውጡን የሚያስቀጥሉና የዜጎች ሁለንትናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ውሳኔዎች እንደሚተላለፉ እንጠብቃለን ብለዋል። የሶህዴፓ ተወካይ አቶ አህመድ ሽዴ በበኩላቸው የተፈጠሩት ተስፋ ሰጪ አገራዊ ለውጦች እንዲቀጥሉ የሚያጋጥሙ ችግሮችን እየፈታን አብረን እንሰራለን ብለዋል። በጉባኤውም የአጋር ድርጅቶችን ሚና ከፍ የሚያደርግና አብሮ ለመስራት አመቺ የሆኑ ውሳኔዎች እንደሚጠብቁም ተናግረዋል። የሀብሊ ተወካይ አቶ አደሪን በድሊ በበኩላቸው በጉባኤው የህግ የበላይነት ማስከበርና ለውጡን ማስቀጠል የሚያስችሉ ውሳኔዎች እንጠብቃለን የሚል ንግግር አድርጓል። ከዚህ በተጨማሪ ሀብሊ በውስጡ እያደረገው ያለው ሪፎርም ውጤታማ እንዲሆን የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ድጋፉን እንዲሰጥም ጠይቀዋል። የጋህዴን ተወካይ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር በአገሪቱ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ያደረገው የስልጣን ሽግግር ታሪካዊ መሆኑን ተናግሯል። በጉባኤውም የሁሉም የአገሪቱ ህዝቦች ሰላምና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ውሳኔዎችን ተግባራዊ ለማድረግ አብረን እንሰራለንም ብለዋል።