በሽራሮ፣ ሽሬ፣ አክሱምና አድዋ ሆስፒታሎችን ጨምሮ 90 የጤና ተቋማት ስራ ጀምረዋል - ኢዜአ አማርኛ
በሽራሮ፣ ሽሬ፣ አክሱምና አድዋ ሆስፒታሎችን ጨምሮ 90 የጤና ተቋማት ስራ ጀምረዋል
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 9/2015 የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ በሽራሮ፣ ሽሬ፣ አክሱምና አድዋ ሆስፒታሎችን ጨምሮ 90 የሚሆኑ የጤና ተቋማት ስራ ጀምረዋል።
በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ በትግራይ ክልል የአገልግሎት ሰጪ ተቋማትና ሌሎችም ተቋማት በፍጥነት ወደ ሥራ መመለስ ችለዋል።
በሰላም ስምምነቱ መሰረት መንግሥት የገባውን ቃል በማክበር የባንክና የቴሌኮም አገልግሎት፣ የጤና ተቋማትና የአየር ትራንስፖርትን ጨምሮ በፍጥነት ሥራ እንዲጀምሩ ማድረግ ችሏል።
በተደረሰው የሰላም ስምምነት መሰረት ተቋማት የተፋጠነ እና ቀልጣፋ አገልግሎት በመጀመራቸው መደሰታቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው ታካሚዎች ገልጸዋል።
በሽሬ ከተማ ስሑል ሆስፒታል በሕክምና ላይ ያገኘናቸው ታካሚዎች በተገኘው ሰላም ከማንም በላይ ሕብረተሰቡ ተጠቃሚ መሆኑንና ደስተኛ ስለመሆናቸውም ተናግረዋል።
በሆስፒታሎችና የጤና ተቋማት የተሻለ የሕክምና አገልግሎትና የመድኃኒት አቅርቦት ጭምር በመኖሩ ከህፃናት እስከ አዋቂ ሕክምና እያገኘን ነው ብለዋል። በግጭቱ ወቅት በተለይም በህፃናት፣ ሴቶችና አቅመ-ደካሞች ላይ ችግሩ የበረታ እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ላይ ሰላማችንን በማግኘታችን ተደስተናል ሲሉ ተናግረዋል።የሰላም ስምምነቱ በትግራይ ክልል በብዙ ችግሮች ውስጥ ለነበረው ሕዝብ ትልቅ እፎይታ የሰጠ መሆኑንም ገልጸዋል።
የሰላም ጉዳይ ከምንም በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው የሰው ልጆች ወሳኝ ነገር ስለመሆኑ በግጭቱ ወቅት ያጋጠሙን ፈተናዎች ብዙ ነገር ያስተማራቸው መሆኑንም ይናገራሉ።የስሑል ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ገብረሕይወት ለገሰ፤ የሆስፒታሉ አገልግሎት መስጠት መጀመር በአካባቢው ለሚኖሩ ከ1 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ትልቅ እፎይታ የሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።
የሆስፒታሉን ሥራ መጀመር ተከትሎ አሁን ላይ በርካታ አገልግሎት ፈላጊዎች በመኖራቸው መጨናነቅ ቢኖርም አሁን ባለው የሰው ኃይል በከፍተኛ ርብርብ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በጤና ሚኒስቴር የሽራሮ፣ ሽሬ፣ አክሱም እና አድዋ ቀጣና የጤና ዘርፍ አስተባባሪ ሳሙኤል ድንቅነህ፤ ከጥቅምት 21 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በርካታ የጤና ተቋማት ወደ ሥራ መግባታቸውን ጠቅሰዋል።
የመድኃኒት አቅርቦት ተደራሽ እየተደረገ መሆኑን የተናገሩት አስተባባሪው የጤና ባለሙዎችም ወደ ሥራ ገበታቸው በመመለስ ሕብረተሰቡ የተቀላጠፈ የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኝ እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
በየወረዳዎች ያሉ ጤና ጣቢያዎችና ሆስፒታሎች ወደ ተሟላ አገልግሎት እንዲገቡ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ መንግሥት በትግራይ ክልል የሰብዓዊ አቅርቦትን በስፋት ተደራሽ ከማድረግ ባለፈ የመልሶ ግንባታና መሰረታዊ አገልግሎቶች ሥራ እንዲጀምሩ ማድረግ ችሏል።