የጥምቀት በዓል የኢትዮጵያ መልካም ገጽታ የሚንጸባረቅበት ነው

አዲስ አበባ ጥር 09 ቀን 2015 (ኢዜአ) የጥምቀት በዓል የኢትዮጵያ መልካም ገጽታ የሚንጸባረቅበት በመሆኑ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ጠብቆ በሰላም እንዲከበር ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ የአዲስ አበባ ሀገረ-ስብከት ሊቀ-ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሔኖክ ጥሪ አቀረቡ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በየዓመቱ ከምታከብራቸው ዘጠኝ ዓበይት በዓላት መካከል ጥምቀት አንዱ የአደባባይ በዓል አድርጋ ስታከብር ቆይታለች።

ከ1ሺህ 500 ዓመታት በፊት የአደባባይ በዓል ሆኖ ሲከበር የቆየው የጥምቀት በዓል ጃንሜዳን ጨምሮ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ከከተራ ቀን ጀምሮ ይከበራል።

ብጹዕ አቡነ ሔኖክ የ2015 ዓ.ም የጥምቀት በዓልን አስመልክተው ለእምነቱ ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን በጠበቀ መልኩ እንዲከበር የአዲስ አበባ ሀገረ-ስብከት ዝግጅቱን ማጠናቀቁንም ገልጸዋል።

የጥምቀት በዓልን በሰላም ለማክበር ከፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰሩ እንደሚገኙ ብጹዕነታቸው ጠቅሰዋል።

ለሃይማኖቱ ተከታይ ወጣቶች ባስተላለፉት መልዕክትም የሰንበት ትምህርት ቤትና መንፈሳዊ ማኅበራት ከፀጥታ አካላት ጋር በመግባባትና በመናበብ በዓሉን በሰላም እንዲያከብሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የጥምቀት በዓል ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አልፎ የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ የሚያንጸባርቅ መሆኑን አመልክተዋል።

የጥምቀት በዓል የኢትዮጵያውያን የጋራ በዓል በመሆኑ ሌሎች ቤተ-እምነቶች በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን እንዲወጡ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም