የረዳት ፕሮፌሰር ሀርቃ ሀሮዬ የቀብር ስነ-ስርዓት ተፈጸመ - ኢዜአ አማርኛ
የረዳት ፕሮፌሰር ሀርቃ ሀሮዬ የቀብር ስነ-ስርዓት ተፈጸመ
ሀዋሳ (ኢዜአ) ጥር 9/2015 የቀድሞ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልና የፍትህ ሚንስትር የነበሩት ረዳት ፕሮፌሰር ሀርቃ ሀሮዬ የቀብር ስነ-ስርዓት የሲዳማ ክልል ከፍተኛ አመራሮችና ወዳጅ ቤተሰቦቻቸው በተገኙበት በሀዋሳ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ- ክርስቲያን ተፈጸመ።
ረዳት ፕሮፌሰር ሀርቃ በሲዳማ ክልል ሀገረ-ሰላም ወረዳ ጋሴ ቀበሌ በ1941 ዓ.ም እንደተወለዱ በቀብር ሥነ ስርዓታቸው ላይ ተገልጿል።
የመጀመሪያና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በተወለዱበት አካባቢ በሚገኙ ኖርዌይ ሉትራን ሚሲዮን እና በደጃዝማች ባልቻ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በይርጋለም አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል።
ከዛም ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመግባት በህግ የመጀመሪያና የሁለተኛ ዲግሪያቸውን እንዳገኙ በቀብር ሥነ-ስርዓቱ ላይ በተነበበው የሕይወት ታሪካቸው ተገልጿል።
ረዳት ፕሮፌሰር ሀርቃ የደርግ ስርዓትን በመቃወማቸው ምክንያት በተለያዩ ጊዜያት ለእስርና ለስደት ተዳርገው እንደነበርም ይሄው ታሪካቸው ያስረዳል።
በስደት በነበሩበት ኬንያም የምስራቅ አፍሪካ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማህበር አባል በመሆን ስርዓቱን ሲቃወሙ እንደነበር ተመላክቷል።
ረዳት ፕሮፌሰር ሀርቃ ከ1993 እስከ 1997 እንዲሁም ከ1998 እስከ 2002 ዓ.ም ለሁለት የምክር ቤት ዘመን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል በመሆንም ሀገራቸውንና ህዝባቸውን አገልግለዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በፍትህ ሚኒስቴር በሚኒስትርነት፣ በንግድ ሥራ አመራር ኮሚሽን በኮሚሽነርነት፣ በኮሜሳ አስተባባሪነት፣ በሲቪል ሰርቪስ፣ በአዲስ አበባ እና በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲዎች በመምህርነት እንዲሁም ለኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን የቦርድ ሰብሳቢ ሆነው አገልግለዋል።
ረዳት ፕሮፌሰር ሀርቃ ሀሮዬ ባደረባቸው ሕመም በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ጥር 6 ቀን 2015 ዓ.ም በ74 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
ረዳት ፕሮፌሰር ሀርቃ ባለትዳር ሲሆኑ የሦት ወንዶች እና የሁለት ሴት ልጆች አባት ነበሩ።
የቀብር ሥርአታቸው ቤተሰቦቻቸው፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸው፣ እንዲሁም በብልጽግና ፓርቲ የሲዳማ ክልል ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አብርሃም ማርሻሎ፣ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ጸጋዬ ቱኬን ጨምሮ ሌሎች የሥራ ሃላፊዎች በተገኙበት ዛሬ በሀዋሳ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ-ክርስቲያን ተፈጽሟል።