ቀጥታ፡

ከ17 ነጥብ 8 ሚሊዮን ለሚበልጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች በሠላም እሴት ግንባታና ወቅታዊ ጉዳዮች ያተኮረ ስልጠና ተሰጥቷል

አዳማ መስከረም 23/2011 በመላ አገሪቱ ከ17 ነጥብ 8 ሚሊዮን ለሚበልጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች በሠላም እሴት ግንባታና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መስጠቱን የፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር አስታወቀ። ሚኒስቴሩ በ2010 ከኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ያከናወናቸውን ተግባራት ለመገምገምና በ2011 እቅድ ላይ ለመምከር ለሶስት ቀናት ያዘጋጀው አገር አቀፍ የውይይት መድረክ ከትናንት ጀምሮ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው። በሚኒስቴሩ የሃይማኖትና እምነት ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ ጌታዋ ደስታው በዚህ ወቅት እንደተናገሩት ስልጠናው የተሰጠው ከሁለቱ ከተማ መስተዳድሮችና ከሁሉም ክልሎች ለተውጣጡ የመንግስትና የሃይማኖት ተቋማት አመራሮች፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣ ለሴቶችና ወጣቶች አደረጃጀቶች ነው። ስልጠናው ያተኮረው በሰላም አብሮ የመኖር እሴት ግንባታ፣ በማህበረሰብ ተኮር ፀረ-አክራሪነት፣ ሴኩላሪዝም፣ ሃይማኖትን ሽፋን ያደረገ አክራሪነትና ጽንፈኝነት ላይ ነው። እንዲሁም በሃይማኖት ነክ ህገ መንግስታዊ ድንጋጌዎችና በሃይማኖት ተቋማት መካከል ጤናማ ግንኙነት የሚያሰፍኑ ሰነዶች ቀርበው  ግንዛቤ እንዲጨበጥባቸው መደረጉን  ገልጸዋል። በዚህም በሁሉም የአገሪቱ አከባቢዎች የተረጋጋ ሰላምን በማስፈን የኢኮኖሚ ዕድገቱን ለማሳለጥ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አቶ ጌታዋ አስረድተዋል፡፡ ሃይማኖትን ሽፋን ያደረገ ፅንፈኝነት ካለው ዓለም አቀፋዊ፣ አህጉራዊና አገራዊ ትስስርና ተለዋዋጭ ባህሪ አንፃር ቀጣይነት ባለው መልኩ ስልጠናው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል። ሚኒስቴሩ ሁሉም የሃይማኖት ተቋማት ህገ መንግስቱን አክብረው መንቀሳቀሳቸውን አስመልክቶ ክትትልና ድጋፍ ማድረጉን የገለጹት ዳይሬክተር ጄኔራሉ፣ ባለፈው ዓመት ለ179 የሃይማኖትና ዕምነት ተቋማት የህጋዊ ሰውነት ፈቃድ መሰጠቱንም አስታውቀዋል። በማህበረሰብ ተኮር ፕሮጀክትም ለ28 ሺህ 733 ወጣቶች የሥራ ዕድል መመቻቸቱን ገልጸዋል። የሐይማኖት ተቋማትን በማስተባበር በኦሮሚያና ሶማሌ ክልል ድንበር በተፈጠረው ችግር ለተፈናቀሉ ወገኖች 20 ነጥብ 3ሚሊዮን ብር ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል። የፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አወል ወግሪስ እንዳመለከቱት ሠላም ለአንድ አገር እድገትና ብልጽግና ወሳኝ በመሆኑ ፀረ-ሰላምና ፀረ-ልማት ተግዳራቶችን ማምከን ከሁሉም አካል ይጠበቃል። በዚህ ረገድ መንግስት አገር በቀል የሆኑ የግጭት መከላከልና አፈታት እንዲሁም የሰላም እሴት ግንባታ አቅምን በመጠቀም ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ ነው ብለዋል። በተለይ ወጣቶችና ሴቶችም በየደረጃው የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮችንና ጠባብ አመለካከት ወቅቱ የሚጠይቀው ተግባርና ኃላፊነት መሆኑን ተገንዝበው ተሳትፎአቸውን እንዲያጠናክሩ አሳስበዋል። የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ የሥራ አስፈፃሚ ቦርድ ተወካይ ንቡረ ዕድ ኤልያስ አብርሃ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቱ ዘርን፣ብሔርንና አመለካከትን መሰረት ያደረገ ክፍፍል፣ግጭትና ሁከት በሰው ሕይወትና አካል ላይ እያደረሱ ያለውን ጉዳት ለመቀልበስ የሃይማኖት ተቋማትና አባቶች ተባብረው ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም