የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የማህበረሰብ ጤና መድህን ለማሻሻል ይሠራል - ኢዜአ አማርኛ
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የማህበረሰብ ጤና መድህን ለማሻሻል ይሠራል
አሶሳ ጥር 09 ቀን 2015 (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኘውን የማህበረሰብ ጤና መድህን አገልግሎት ለማሻሻል በትኩረት እንደሚሰራ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብዲሳ ገለጹ::
የክልሉ የማህበረሰብ ጤና መድህን የ2014 አፈጻጸም እና የ2015 ንቅናቄ መድረክ ዛሬ በአሶሳ ተጀምሯል::
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብዲሳ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የጤና መድህን በተለይም በዝቅተኛ ኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ከድንገተኛ የህክምና ወጪ ይታደጋል::
ይህም በአደጉ አገራት ጭምር ለውጥ ያመጣና ሊወሰድ የሚገባ ተሞክሮ መሆኑንም ተናግረዋል ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ።
በክልሉ በ2008 ዓ.ም የጤና መድን አገልግሎት ቢጀመርም ከ21 ወረዳዎች ውስጥ ተግባራዊ የተደረገው በሶስት ወረዳዎች ብቻ ነው ብለዋል።
በ2015 ተጨማሪ በስድስት ወረዳዎች አገልግሎቱን ለማስፋፋት ጥረት መጀመሩን ጠቅሰዋል።
የጤና አገልግሎት በመንግስት ብቻ ለህብረተሰቡ ማዳረስ እንደማይቻል ገልጸው በየደረጃው የሚገኝ አመራር እና ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን ማበርከት እንዳለባቸው ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አስገንዝበዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጤና ቢሮ ሃላፊ አቶ ፈቃዱ ረጋሳ በበኩላቸው በክልሉ በየደረጃው የሚገኝ አመራር ለጤና መድህን የሰጠው አነስተኛ ትኩረት ከዘርፉ ችግሮች ውስጥ ዋነኛው ነው ብለዋል።
በመድረኩ የክልሉን የጤና መድህን እንቅስቃሴ ለማጠናከር ጠንካራ ውይይት ተደርጎ ለችግሮቹ መፍትሄ ይቀመጣል ተብሎ ይጠበቃል።
በመድረኩ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ፣ የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍሬህይወት አበበ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈጉባኤ ወይዘሮ አለምነሽ ይባስን ጨምሮ ሌሎች አመራሮች እና እንግዶች እየተሳተፉ ነው።