ቀጥታ፡

"የጨበጥነው የፖለቲካ አቋም ያለፈውን ከማፍረስ የሚነሳ ሳይሆን የወደፊቱን አጠናክሮ የሚገነባ ነው" ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ

አዲስ አበባ  መስከረም 23/2011 በአዲሱ የለውጥ እንቅስቃሴ "የጨበጥነው የፖለቲካ አቋም ያለፈውን ከማፍረስ የሚነሳ ሳይሆን የወደፊቱን አጠናክሮ የሚገነባ ነው" ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ዛሬ በተጀመረው 11ኛው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ድርጅታዊ ጉባኤ ላይ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ አሁን ለደረሰችበት ሁኔታ ያለፈው መንገድ መሰረት ነው። በመሆኑም ስለ ትላንቱ አብዝቶ መጨነቅ እና መጠበብ ሳይሆን ነገን በጥንቃቄ መገንባት ነው። ትላንትን መቀየር የማይቻል በመሆኑ ቁርሾዎችን በመፍታት የወደፊት አብሮነትን በማረጋገጥ ላይ ማተኮር ይኖርብናል ሲሉም ተናግረዋል። በዚህም ነገን በማሰብና በትጋት በመስራት ለአዲሱ ትውልድ አዲስ ተስፋን ብቻ ሳይሆን አገርን ማስረከብ ይገባልም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ። እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ "እንደ አገር እና ህዝብ በብዙ ችግሮች የተከበብን በመሆኑ ችግሩ የአገርና የህዝብ መጻኢ እጣ ፈንታ በታሪክ ብቻ አይወሰንም"። የተደረገውን በመደጋገም እና አዲስ ነገር በመጣ ቁጥር "እንዳልተገራ ፈረስ ያዙኝ ልቀቁኝ በማለት" ለውጥን የምንገዳደር ከሆነ አገሪቱ የምትመኘውን ፈጣን እና ሁለንተናዊ ለውጥ ማምጣትና ማረጋገጥ አይቻልም ነው ያሉት። ለስልጣኔ የሚመጥን ዋጋ ለመክፈል ካልተዘጋጀን፣ ስልጣኔ ውድ ነው ካልን ኋላቀርነትን ማስቀረት የማይቻል በመሆኑ ስለወደፊቱ አጠናክሮ ማሰብና በጠነከረ አንድነት መስራት ይገባልም ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም