በአዲስ አበባ ባለፉት ስድስት ወራት 365 ኪሎ ሜትር የመንገድ ጥገና ሥራ ተከናውኗል - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ ባለፉት ስድስት ወራት 365 ኪሎ ሜትር የመንገድ ጥገና ሥራ ተከናውኗል

አዲስ አበባ ጥር 09 ቀን 2015 (ኢዜአ) በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያው ስድስት ወራት 365 ኪሎ ሜትር የመንገድ ጥገና ሥራ ማከናወኑን የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን አስታወቀ።
የባለሥልጣኑ ምክትል ዳይሬክተር እያሱ ሰለሞን ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ባለፋት ስድስት ወራት ለእግረኛና ለተሽከርካሪ አስቸጋሪ የሆኑ መንገዶች ላይ የጥገና ሥራ ተከናውኗል።
ባለሥልጣኑ በተያዘው በጀት ዓመት መጨረሻ 611 ኪሎ ሜትር የሚረዝም መንገድ ላይ የጥገና ሥራዎች ለማከናወን ያቀደ መሆኑን ጠቁመው፤ ባለፉት ስድስት ወራት የዕቅዱን ከግማሽ በላይ ማከናወን መቻሉን አስረድቷል።
ጥገና ከተከናወነላቸው መንገዶች መካከል 263 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የውሃ መተላለፊያ ቱቦ (ድሬኔጅ) መስመር ፅዳት፣3 ኪሎ ሜትር የድሬኔጅ መስመር እድሳት እንዲሁም 39 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ጥገና ሥራ ተከናውኗል።
በተጨማሪም 18 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትሩ ደግሞ የጠጠር መንገድ ጥገና ሥራ የተከናወነመሆኑን አስረድተው፤ የኮብልስቶን ጥገና ሥራም ማከናወኑን አስረድተዋል።
''ከጥገና ስራዎች አንጻር በ2015 በጀት ዓመት እንደአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ 611 ኪሎ ሜትር የሚደርስ ልዩ ልዩ የመንገድ ጥገና ስራዎች ለማከናወን እቅድን ነው ያለነው።
ይህን ወደ ስድስት ወራት ስናመጣው በመጀመሪያ ስድስት ወር ውስጥ 352 ኪሎ ሜትር አካባቢ የሚደርስ ልዩ ልዩ የመንገድ ጥገና ስራዎች አቅድን ስንስራ ቆይተናል።
በአጠቃላይ አፈጻጸም ወደ 365 ኪሎ ሜትር አካባቢ የሚደርስ ማከናወን ችልናል።
ከዚህ ውስጥ ወደ 39 ኪሎ ሜትር አካባቢ የሚደርሰው የአስፓልት መንገድ ጥገና ነው።
ባለፋት ስድስት ወራት የጠጠር መንገዶች የኮብልስቶን መንገዶች ጥገና እንደዚሁም የእግረኛ መንገዶችንም እንደዚሁ የማከናወን ስራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል።
'' በበጀት ዓመቱ ማጠናቀቂያ ጊዜያት ቀሪውን የመንገድ ጥገና በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ለማከናወን ርብርብ እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የመንገድ ብልሽት ለትራፊክ ፍሰቱ ምቹ ያለመሆንና በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ላይ አሉታዊ ጫና የሚያደርስ መሆኑ ሁሉም ሊገነዘበው ይገባል ብለዋል።

ስለዚህም ሕብረተሰቡ ለመንገድ ሃብት ተገቢውን እንክብካቤ በማድረግ የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ አክለዋል።
መንግሥት ከፍተኛ ወጪ በማውጣት አዳዲስና ነባር መንገዶች ላይ ጥገና እንደሚያደርግ በማስታወስ መንገዶች በአሸከርካሪዎችና በሕብረተሰቡ ጥንቃቄ ጉድለት ብልሽት ይገጥማቸዋል ብለዋል።
ሦስት አዳዲስ የመንገድ ፕሮጀክቶች የውል ስምምነታቸው ተጠናቆ በበጀት ዓመቱ ሥራቸውን ለመጀመር የዝግጅት ምዕራፍ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።
ቀደም ብሎ የተጀመሩ የመንገድ ፕሮጀክቶች ቅድሚያ ሰጥቶ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
''በዚህ ዓመት የውል ስራቸው የተጠናቀቀ መንገድ ፕሮጀክቶች ወደ ሶስት አካባቢ የሚደርሱ አሉ።
እነዚህም በአጠቃላይ ስራዎችን ማስጀመር ከሚያስችሉ የወሰን ማስከበር ስራዎች ጎን ለጎን እየተሰሩ ያሉበት ሁኔታ አለ።
አንደኛው ከአየር ጤና ወለቴ የሚወስድው መንገድ ነው።
እዛ አካባቢ ሰፊ የህብረተሰቡ የመንገድ የልማት ጥያቄ ነበረ ሌላኛው መውጫ መግቢያ ኮሪደርም ከሆኑ ቦታዎችም የአየር ጤና ወለቴ መንገድ ነው ።
ይህም የመንገድ ፕሮጀክት በቀጥታ ወደ ግንባታ ለማስገባት ከወሰን ማስከበር ስራዎች ጎን ለጎን ግንባታ እየተከናወነ ያሉበት ሁኔታ አለው።
እንደዚሁም ደግሞ ከቦሌ ኤድናሞል ወደ እንግሊዝ ኤምባሲ አካባቢ አቅጣጫ እንደዚሁ ደሞ በማስፋፊያ ቀደም ብሎ የነበረ ፕሮጀክት በማስፋፊያ ደረጃ የሚከናወን የመንገድ ፕሮጀክት አለን።''