ቀጥታ፡

በድሬደዋ የከተራና የጥምቀት በዓላት በሠላም እንዲከበሩ ዝግጅት ማደረጉን ፖሊስ አስታወቀ

ድረዳዋ (ኢዜአ) ጥር 9/2015 በድሬዳዋ አስተዳደር የከተራና የጥምቀት በዓል ያለምንም የፀጥታ ችግር በሠላም እንዲከበር ዝግጅት ማድረጉን ፖሊስ አስታወቀ።

የጥምቀት በዓልን በፍቅርና በአንድነት ለማክበር ለአንድ ወር ያህል ዝግጅት ሲያደርጉ መቆየታቸውን የገለጹት ደግሞ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን የድሬዳዋ ሀገረ ስብከት ስራ አስኪያጅ ናቸው።

የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ዋና ኮሚሽነር አለሙ መግራ፤ የከተራና የጥምቀት በዓላት ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበሩ የፀጥታ ተቋማት አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን ለኢዜአ ተናግረዋል።

ፖሊስ ከድሬዳዋ ሀገረ ስብከት ጽህፈት ቤት፣ በየቀበሌው ከሚገኙ የወጣቶችና የማህበረሰብ  አቀፍ ፖሊስ አደረጃጀቶች ጋር በመቀናጀት ፀጥታውን የማስጠበቅ ስራ እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።

በበዓሉ በወቅት ህግና ስርዓት እንዲጠበቅ የጋራ መግባባት መፈጠሩን ዋና ኮሚሽነር አለሙ አስረድተዋል።

እንደ ዋና ኮሚሽነሩ ገለፃ፤ በበዓላቱ ወቅት በከተማው ምንም ዓይነት የትራፊክ አደጋ እንዳይከሰት የሚያስችል አደረጃጀት ተፈጥሮ ወደ ስራ ተገብቷል።

በዓላቱ በሰላም እንዲከበሩ ለማስቻል ታቦታቱ ከመንበራቸው ከሚነሱባቸው አካባቢዎች ከሚገኙ ወጣቶችና የባጃጅ ታክሲ አሽከርካሪዎች ጋር በመወያየት ለበዓሉ በሰላም መከበር ምቹ ሁኔታ መፍጠር መቻሉን አብራርተዋል።

የድሬዳዋ ሀገረ-ስብከት ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ መላከ ኃይል አባ ተስፋዬ እማምሰው በበኩላቸው፤ በአለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና የተሰጠው የሁሉም ኢትዮጵያዊ በዓል የሆነው ጥሞቀት በደመቀ አንድነት፣ ፍቅርና መተጋገዝ እንዲከበር ከሌሎች ኃይማኖት ተቋማትና የፀጥታ አካላት ጋር  በቅንጅት እየተሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የሀገረ ስብከቱ ጽህፈት ቤት በዓላቱ ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበሩ በየአድባራቱ ከሚገኙ የሰንበት ትምህርት ቤቶች ወጣቶችና መዘምራን ጋር የፀጥታ ጉዳይን አስመልክቶ አስፈላጊውን ዝግጅት ሲደርጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል ።

የጥምቀት በዓል ስናከብር የተቸገሩትን ና የታመሙ ወገኖች በመርዳት፣ በተለያዩ ምክንያቶች ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች በማሰብና በመደገፍ እንዲሆንም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የታክሲ አሽከርካሪ ወጣት ደረጀ ሽመልስ በሰጠው አስተያየት፤ ለበዓላቱ ብቻ ሳይሆን ሁልጊዜም የድሬደዋን ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ በማህበር ተደራጅተው ኃላፊነታቸውን እየተወጡ መሆኑን ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም