ቀጥታ፡

የደቡብ ፖሊስ ኮሚሽን የከተራና የጥምቀት በዓል በሰላም እንዲከበር ተዘጋጅቷል

ሐዋሳ ጥር 9 ቀን 2015 (ኢዜአ). በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል የከተራና የጥምቀት በዓል በሰላም እንዲከበር ዝግጅቱን አጠናቆ ወደ ሥራ መግባቱን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር አለማየሁ ማሞ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት የጥምቀት በዓል በዓለም ቅርስነት የተመዘገበ የሀገሪቱ ታላቅ በረከት ስለሆነ በታላቅ ድምቀት እንዲከበር በጸጥታው ረገድ ቅድመ ዝግጅት ተደርጎ ስራ ውሰጥ ተገብቷል።

የውጭ ሀገር ቱሪስቶች ጭምር የሚታደሙበት ታላቅ በዓል እንደመሆኑ መጠን የከተራና የጥምቀት በዓላት ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም እንዲከበር ከበዓሉ አዘጋጅ ኮሚቴና ከፍትህ አካላት ጋር እቅድ በማውጣትና በመናበብ በየደረጃው እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።

በክልሉ 1 ሺህ 913 ታቦታት በከተራው እለት ወደ ባህረ ጥምቀቱ እንደሚጓዙ ገልጸው ታቦተ ህጉ በሰላም ወጥቶ በሰላም እስኪመለስ ድረስ ጠንካራ የፀጥታ ማስከበር ስራ እንደሚከናወን ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ በዓላቱ በሰላም ተጀምረው እንዲጠናቀቁ ለወንጀል እና ትራፊክ አደጋ መከላከል ተግባሩ ላይ ልዩ ትኩረት በመስጠት በርካታ የሰው ኃይል ማሰማራቱንም ጠቅሰዋል ኮሚሽነሩ።

በታቦት ማደሪያ ስፍራዎች፣በተለይም በአደባባይ የሚከበር በዓል ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የበዓሉ ታዳሚዎች ላይ የስርቆት ወንጀልና የፀጥታ ችግር እንዳያጋጥማቸው በባህረ ጥምቀቱ አካባቢና አማካኝ ስፍራዎች ጊዜያዊ ፖሊስ ጣቢያ ተከፍተው አገልግሎት የሚሰጡበት ሁኔታ መመቻቸቱን አውሰተዋል።

ችግሮች ሲከሰቱም በየደረጃው የሚገኘው የፖሊስ አባላት በአስቸኳይ ምርመራ አጣርቶ ወዲያው ምላሽ እንዲያገኝ የፍትህና ዐቃቢ ህግ ጽህፈት ቤቶች በበአላት ቀናት ክፍት ሆነው አገልግሎት እንደሚሰጡም አስታውቀዋል።

ምእመናኑ ከስፍራ ወደ ስፍራ ሲንቀሳቀሱ የትራፊክ አደጋ እንዳይከሰት ዋና ጎዳናዎች ክፍት መደረጋቸውንና አማራጭ መንገዶችም ከመሰናዳታቸው ባሻገር የትራንስፖርትና የትራፊክ ፖሊስ አባላት የተቀናጀ ስምሪት መሰጠቱን አስታውቀዋል።

በክልሉ በተለየ ሁኔታ በዓሉ ከጥር 10 እስከ 18 ቀን 2015 ድረስ የሚቆይ መሆኑን ያነሱት ኮሚሽነሩ ቀድመው የሚገቡትም ሆነ የሚቆዩ ታቦታት በሰላም ወደ ማረፊያቸው እንዲደርሱ ለማድረግ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጎ ተግባራዊ ስራ ውስጥ መግባቱን አብራርተዋል።

የእምነቱ ተከታዮች በተለይም ወጣቶች ከዚህ በፊት እንደሚያደርጉት ሁሉ በተደራጀ መንገድ ከፖሊስ እና ከሌሎች ፀጥታ አካላት ጎን በመቆም ለበዓሉ በሰላም መከበር የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል።

የበዓሉ ታዳሚ ምዕመናንና መላው ህብረተሰብ በማንኛውም ወቅት ከፀጥታ ስራ ጋር ተያያዥ እና አጠራጣሪ ነገሮች ሲመለከት በአቅራቢያው ለሚገኝ የፀጥታ አካላት ጥቆማ እንዲሰጥ ኮሚሽነር አለማየሁ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም