የብሔራዊ ቡደኑ ተጫዋቾች ለአልጄሪያው ጨዋታ በሙሉ የራስ መተማመን ላይ ይገኛሉ-አሰልጣኝ ውበቱ አባተ

74

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 9/2015 “ተጫዋቾቼ ለአልጄሪያው ጨዋታ በሙሉ የራስ መተማመን ላይ ይገኛሉ፤ያላቸውን ሁሉ ለመስጠት ዝግጁ ናቸው” ሲሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ገለጹ።

በአገር ውስጥ ሊግ የሚገኙ ተጫዋቾች ብቻ የሚሳተፉበት 7ኛው የአፍሪካ አገራት እግር ኳስ ሻምፒዮና(ቻን) በአልጄሪያ አስተናጋጅነት በመካሄድ ላይ ነው።

በምድብ አንድ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሁለተኛ ጨዋታውን ዛሬ በኔልሰን ማንዴላ ስታዲየም ከአዘጋጇ አገር አልጄሪያ ጋር ከምሽቱ 4 ሰአት ጨዋታውን ያደርጋል።

የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ እና አምበሉ መስዑድ መሐመድ የዛሬውን ጨዋታ አስመልክቶ ትናንት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

አልጄሪያ በሜዳው እና በደጋፊው ፊት መጫወቱ እንዲሁም ከኛ አንጻር ከመጀመሪያው ጨዋታ የተሻለ የማገገሚያ ጊዜ ማግኘታቸው ጨዋታውን ፈታኝ እንደሚያደርገው አሰልጣኝ ውበቱ ገልጸዋል።

ፈታኝ ሁኔታዎች ቢኖሩም ያለንን አቅም ተጠቅመን ከጨዋታው የተሻለ ውጤት ለማግኘት እየተዘጋጀን እንገኛለን፤ ተጫዋቾቼ በሙሉ የራስ መተማመን ላይ ይገኛሉ ብለዋል።

ከሞዛምቢኩ ጨዋታ የተወሰነ የታክቲክ ለውጥ ሊያደርጉ እንደሚችሉም ፍንጭ ሰጥተዋል።

ከሞዛምቢክ ጋር በነበረው ጨዋታ ጉዳት ያጋጠመው ወንድማገኝ ኃይሉ ለነገው ጨዋታ እንደማይደርስ አስልጣኝ ውበቱ አረጋግጠዋል።

ጉልበቱ ላይ እብጠት ያጋጠመው ወንድማገኝ የጉዳቱ መጠን ገና እንዳልታወቀ ተናግረዋል።

ከወንድማገኝ ውጪ ሌሎቹ ተጫዋቾች በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙም ገልጸዋል።

የቻን ውድድር በአገር ውስጥ ሊግ ለሚጫወቱ ተጫዋቾች በብሔራዊ ቡድን የመጫወት እድል እንዲያገኙ መልካም አጋጣሚን ፈጥሯል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አምበል መስዑድ መሐመድ የአልጄሪያው ጨዋታ ከሞዛምቢኩ የተለየ ነው፤ ለጨዋታው በአካል እና በአዕምሮም እየተዘጋጀን ነው ብሏል።

በመጀመሪያው ጨዋታ እንዳገኘናቸው የግብ እድሎች መፍጠር ከቻለን እና ወደ ግብ ከቀየርን ጥሩ ውጤት የማስመዝገብ እድል ይኖረናል ብዬ አምናለሁ ሲል ገልጿል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከአልጄሪያ ጋር ከሚያደርገው የቻን ሁለተኛ የምድብ ጨዋታ የመጨረሻ ልምምዱን ትናንት ማምሻውን አከናውኗል።

ዋልያዎቹ በመጀመሪያ የምድብ ጨዋታቸው ከሞዛምቢክ ጋር ያለ ምንም ግብ አቻ መለያየታቸው የሚታወስ ነው።

የቻን ውድድር አዘጋጅ የሆነው የአልጄሪያ ብሄራዊ ቡድን በምድቡ ባደረገው የመጀመሪያ ጨዋታ ሊቢያን 1 ለ 0 ማሸነፏ ይታወሳል።

ኢትዮጵያ እና አልጄሪያ እርስ በእርስ ሲገናኙ የዛሬውን ጨምሮ ለዘጠነኛ ጊዜ ነው።

አልጄሪያ አራት ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዛለች።

ኢትዮጵያ አንድ ጊዜ አሸንፋለች። ሶስት ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።

በስምንቱ ጨዋታዎች አልጄሪያ 18 እንዲሁም ኢትዮጵያ 9 ግቦችን አስቆጥረዋል።

ኢትዮጵያ አልጄሪያን ያሸነፈችው እ.አ.አ 1968 ራሷ ባዘጋጀችው ስድስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ነበር።

በወቅቱ ሁለቱ አገራት በምድብ አንድ ባደረጉት ጨዋታ ኢትዮጵያ በመንግስቱ ወርቁ፣ በሸዋንግዛው አጎናፍር እና በሉቺያኖ ቫሳሎ ግቦች አልጄሪያን 3 ለ 1 አሸንፋለች።

ቡአሌም አሚሩቼ ለአልጄሪያ በወቅቱ ግቧን ያስቆጠረ ተጫዋች ነበር።

በምድብ አንድ ዛሬ ሞዛምቢክ ከሊቢያ በኔልሰን ማንዴላ ስታዲየም ከምሽቱ 1 ሰአት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ትናንት በተደረጉ የቻን ውድድር ጨዋታዎች በምድብ አምስት ካሜሮን ኮንጎ ብራዛቪልን 1 ለ 0 ስትረታ በምድብ አራት ማሊ ከአንጎላ ሶስት አቻ ተለያይተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም