ቀጥታ፡

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቤተ-እስራኤላውያንን ታሪክ፣ ባህል፣ ቅርስና ቋንቋን የሚያስተዋውቅ የምርምር ሙዚየም ሊቋቋም ነው

ጎንደር (ኢዜአ) ጥር 9/2015 የቤተ-እስራኤላውያንን ታሪክ፣ ባህል፣ ቅርስና ቋንቋን የሚያስተዋውቅ የምርምር ሙዚየም በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሊቋቋም መሆኑ ተገለጸ።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ምሁራንና ከእስራኤል ሀገር የመጡ ምሁራን የሚሳተፉበት የኢትዮጵያና የእስራኤል የታሪክ ትስስር ዓለም አቀፍ ሲፖዚየም በጎንደር ዩኒቨርሲቲ እየተካሔደ ነው።

በእስራኤል የኢትዮጵያ አምባሳደር ረታ አለሙ በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልእክት ኢትዮጵያና እስራኤል ጠንካራ ትስስር ያላቸው አገራት መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የሙዚየሙ መመስረትም የሁለቱን ሀገራት የባህል እሴቶች ለማጠናከር ብሎም ለጋራ ልማትና ተጠቃሚነት እንዲሁም የሕዝቦችን ትብብር ለማሳደግ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከዚህ ቀደም እስራኤል ሀገር ከሚገኙ አቻ የትምህርት ተቋማት ጋር በምርምርና በቴክኖሎጂ ሽግግር ዘርፍ የተሻለ ግንኙነት መስርቶ መቆየቱን አስታውሰውዋል፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አስራት አጸደወይን በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የሁለቱን ሀገራት ታሪክ፣ ባህልና የኢኮኖሚ ግንኙት የሚያጠናክሩ ትስስሮችን እስራኤል አገር ከሚገኙ አቻ የትምህርትና የምርምር ተቋማት ጋር በትብብር እየሰራ ነው ብለዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት ዩኒርቨርሲቲው በህክምና፣ በግብርና፣ በቴክኖሎጂና በባለሙያዎች አቅም ግንባታ ዘርፍ እስራኤል ሀገር ከሚገኙ አቻ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በትብብር ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡

ወደፊትም ይህን የአቻ ግንኙነት ለማጠናከር እንዲቻል የሁለቱ ሀገራት ምሁራን በትብብር እንዲሰሩ ጥረት ይደረጋል ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ካሳሁን ተገኘ እንደገለጹት በጎንደርና አካባቢው ቤተ-እስራኤላውያን የኢኮኖሚ፣ የባህልና የቴክኖሎጂ አበርክቶ ከፍተኛ ነው፡፡

የሚቋቋመው ሙዚየም የሁለቱን ሀገራት ታሪካዊ ትስስር የሚያጠናክርና በእስራኤል ሀገር የተወለዱ ቤተ-እስራኤላውያን ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት እንዲመራመሩ የሚያግዝ መሆኑን ገልፀዋል።

ሙዚየሙ የቤተ-እስራኤላውያኑ የቀደመ ታሪክ፣ ባህል፣ ቅርስና ቋንቋ ተሰንዶ የሚቀመጥበትና ምርምር ማድረግ የሚሹ የሀገር ውስጥም ሆነ የእስራኤል ምሁራን የተሟላ የታሪክ ግብዓት የሚያገኙበት መሆኑን ተናግረዋል።

የሙዚየሙ መመስረቻ መመሪያ ቀርቦ ውይይት የሚደረግበት ሲሆን ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ወደ ትግበራ እንደሚገባም ገልፀዋል።

ለሶስት ቀናት በሚቆየው ሲምፖዚየም የጎንደር ዩኒቨርሲቲ መምህራንን ጨምሮ በእሰራኤል ሀገር በሚገኙ የከፍተኛ የትምህርትና ምርምር ተቋማት የሚሰሩ 20 ያህል እስራኤላውያን ምሁራን በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡

በሲምፖዘየሙ የቤተ-እስራኤላውያን አበርክቶ እንዲሁም የኢትዮጵያና የአስራኤል ታሪካዊ ግንኙነቶች በሚሉ ርዕሶች ዙሪያ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው ከወጣው መርሃ-ግብር ለማወቅ ተችሏል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም