ቀጥታ፡

መንግስት በታንዛኒያ በእስር ቤቶች የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞችን ለመመለስ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሰራ ነው

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 8 ቀን 2015 መንግስት በታንዛኒያ በእስር ቤቶች የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞችን ለመመለስ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን በታንዛንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሽብሩ ማሞ ገለጹ።

በህገ-ወጥ ደላሎች ተታለው በርካታ ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች በኬኒያ በኩል አድርገው ወደ ደቡብ አፍሪካ ለማቅናት ሲሞክሩ ይስተዋላል፡፡

በዚህም ሞትን ጨምሮ እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ይጋፈጣሉ፤ በርካቶች ደግሞ በሚያልፉባቸው አገራት በቁጥጥር ስር ውለው ለእስር ተዳርገዋል፡፡

በታንዛኒያና ማላዊ እስር ቤቶች የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ደግሞ በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በታንዛንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሽብሩ ማሞ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ጥቂት የማይባሉ ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለሚሄድ እጅግ አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ያልፋሉ፡፡

በዚህም በተለያዩ ጊዜያት በታንዛኒያ በኩል አድርገው በማላዊ ድንበር ወደ ደቡብ አፍሪካ በህገ-ወጥ መንገድ ለመሻገር ሲንቀሳቀሱ የተገኙ 5 ሺህ ኢትዮጵያዊያን በታንዛንያ መንግስት በቁጥጥር ስር ውለው ለእስር መዳረጋቸውን አስታውሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ከዓለም አቀፍ የፍልሰት ድርጅት ጋር በመተባበር በተያዘው ዓመት 1 ሺህ 99 የሚሆኑትን ከታንዛኒያ እስር ቤቶች ወደ አገር ቤት መመለሱን ገልጸዋል።

በቀጣይም መንግስት በታንዛኒያ በእርስ ቤቶች የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞችን ለመመለስ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን በዘላቂነት ለመግታት በኬንያና ኢትዮጵያ እንዲሁም በኬንያና በታንዛንያ ድንበር አካባቢ ጠካራ የቁጥጥር ስራ ለመስራት አገራቱ መስማማታቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪም በአገር ውስጥ የስራ እድል ፈጠራን በማጎልበትና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን በማከናወን ህገ-ወጥ ስደትን ለመከላከል ይሰራል ነው ያሉት፡፡

በተያያዘ ኢትዮጵያና ታንዛንያ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን ጠቅሰው፤ የሁለትዮሸ ግንኙነቱን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማሸጋገር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሁለቱ ሀገራት በጸረ-አፓርታይድ ትግልና በፓንአፍሪካኒዝም ንቅናቄ ጠንካራ ወዳጅነት እንደነበራቸው ያስታወሱት አምባሳደር ሽብሩ፤ አሁን ላይ አገራቱ በበርካታ መስኮች ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር በቁርጠኝነት እየሰሩ ነው ብለዋል፡፡  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም