የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ለሀዋሳ ሜሪ ጆይ አረጋውያን ማዕከል የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ለሀዋሳ ሜሪ ጆይ አረጋውያን ማዕከል የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ
ሀዋሳ (ኢዜአ) ጥር 8/2015 የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በሀዋሳ ሜሪ ጆይ አረጋውያን ማዕከል ለተጠለሉ አረጋውያን ማዕድ በማጋራት የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።
የቁሳቁስ ድጋፉን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ ለሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ መስራችና ሥራ አስኪያጅ ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ አስረክበዋል።
አገልግሎቱ ያደረገው ድጋፍ 150 ጥንድ አንሶላና የሌሊት ልብስ፣ 75 ሊትር የምግብ ዘይትና የንጽህና መጠበቂያ ቁሶች መሆናቸውን በርክክቡ ወቅት ተገልጿል።
በተጨማሪም አገልግሎቱ በማዕከሉ ለጠለሉ 120 አረጋውያን ማዕድ አጋርቷል።
የአገልግሎቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ በወቅቱ እንደገለጹት፤ አገልግሎቱ ከአረጋውያን ጎን መሆኑን ለማሳየት የተደረገ ድጋፍ መሆኑን ጠቁመው በተለይ በማዕከሉ ያለውን የኤሌክትሪክና ትራንስፎርመር ችግር ለመፍታት ቃል ገብተዋል።
እኛ ኢትዮጵያውያን እርስ በእርስ መደጋገፍ እንደምንችል ማዕከሉን በጎበኘንበት ወቅት ተረድተናል ያሉት አቶ ሽፈራው፤ ይህ ተግባር እንዲስፋፋ የሁሉንም ተሳትፎ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
ሲስተር ዘቢደር በአገልግሎቱ ለተደረገው ድጋፍ በአረጋውያን ስም አመስግነዋል።
በተለይ ማዕከሉ በኤሌክትሪክ ችግር ምክንያት በተለያዩ ለጋሽ አካላት የተገኙ የህክምናና ሌሎችም ማሽኖች ካለ አገልግሎት መቀመጣቸውን አስታውቀዋል።
በዚህ ረገድ ያለው ችግርን ለማቃለል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አጋርነታቸውን በማሳየታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።
አሁን ላይ ማዕከሉን ለማጠናከር የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር፣ በከተማዋ የሚገኙ የመንግሥትና የግል ሴክተሩ የጤና ባለሙያዎች እንዲሁም ከሲዳማ ክልላዊ መንግስት ጋር በቅርበት እየሰሩ መሆናቸውንም አብራርተዋል።