ኢትዮጵያ በሁላችንም ላብ እና ደም የተሰራች ቤታችን ናት-ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በሁላችንም ላብ እና ደም የተሰራች ቤታችን ናት-ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ
አዲስ አበባ መስከረም 23/2011 "ኢትዮጵያ በሁላችንም ላብ እና ደም የተሰራች ቤታችን በመሆኗ ባለቤቶቿም ሁላችንም መሆን አለብን" አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ዛሬ በይፋ በተጀመረው 11ኛው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ድርጅታዊ ጉባኤ ላይ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትላንት የሁላችንም አባት እናቶች ለዚህች አገር ደማቸውን ገብረዋል፤ ዛሬም ሁላችንም አዲሲቷን ኢትዮጵያ በጋራ ልንገነባ ይገባል ነው ያሉት። ዛሬ የተላበስነው ማንነትና አገራዊ አንድነት እንዲኖረን አድርጋ በመደመር መርህ እኛን ሰርታናለችና ይህችን ታላቅ አገር ሁላችንም ካለፍንም በኋላም ቢሆን ኢትዮጵያ "ኢትዮጵያ" ሆና እንድትቀጥል ማድረግ ይገባናል ብለዋል። ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት የለውጥ ሽግግር ቀጣይነት እንዲኖረው "ቀና ልብ እና አርቆ አስተዋይ አዕምሮን ይጠይቃል" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀደመው ትውልድ ልምድ እና ጥበቡን ተጠቅሞ ለአዲሱ ትውልድ የመሪነቱን በትር ሊያስረክብ ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል። የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ዳር እስከዳር ያሉ ኢትዮጵያውያን የሚሳተፉበት ድርጅት እንዲሆንም በጽናት መስራት እንደሚያስፈልግ ነው የገለጹት።