ቀጥታ፡

ኢህአዴግ በ11ኛው ድርጅታዊ ጉባኤው ጠቃሚ ውሳኔዎችን እንደሚያሳልፍ እንጠብቃለን...የትግራይ ምዕራባዊ ዞን ነዋሪዎች

ሁመራ መስከረም 23/2011 የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር/ኢህአዴግ በ11ኛው ድርጅታዊ ጉባኤው በሃገሪቱ ለተፈጠሩ ችግሮች መፍትሔ የሚሆኑ ውሳኔዎችን ያሳልፋል ብለው አንደሚጠብቁ ኢዜአ ያናገራቸው የትግራይ ምዕራባዊ ዞን ነዋሪዎች ገለጹ። በጉባኤው የሚሳተፉ እህት ድርጅቶችና ታዳሚዎች በጥልቀት ተወያይተው የአገሪቷዋን አንድነትና እድገት  የሚያረጋግጡ ውሳኔዎች እንደሚተላለፉበት እምነታቸው መሆኑን የተናገሩት በዞኑ የፀገዴ ወረዳ ነዋሪ አቶ ክፍላይ ዮሃንስ ናቸው። ከአራቱ እህት ድርጅቶች ሁለቱ አርማና ስያሜ መቀየራቸው ምናልባት የትግል አንድነታቸው ላይም ልዩነት እንዳይፈጥር ስጋት እንዳላቸው ተናግረዋል። በመሆኑም አራቱ እህት የኢህአዴግ ድርጅቶች የህዝቦችን የልማትና የሰላም ጥያቄ ለመመለስ የሰከነና የበሰለ ውይይት በማድረግ ጉባኤው በስኬት እንዲጠናቀቅ ተመኝተዋል ። “ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ መስፍን ይሕደጎ በበኩላችው፣ ኢህአዴግ የህዝብ ጥቅም የሚያረጋግጡ ፣ዘላቂ ሰላም የሚያመጡ ውሳኔዎችን በማስተላለፍ ጉባኤውን በድል እንደሚያጠናቅቅ ሙሉ እምነት አለኝ” ብለዋል። “በኢህአዴግ ባለፉት አመታት በልማታዊና ዲሞክራስያዊ መስመር የሚጨበጥ ልማት ተመዝግበዋል” ያሉት አቶ መስፍን፣ እህት ድርጅቶች በሃገራዊ ለውጥና አንድነት የጋራ አቋም ይዘው እንደሚወጡ ያላቸውን እምነት ተናግረዋል። “ኢህአዴግ የጀመረውን ልማት ለማስቀጠልና ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ እንደወትሮው በአንድነት መስራት ይጠበቅበታል”ያሉት ደግሞ  የቃፍታ ሑመራ ወረዳ ነዋሪው አቶ ኪዳነ በሪሁ ናቸው። ጉባኤው ልዩነቶችን በውይይት በመፍታት የህዝቦችን ጥቅም የሚያረጋግጡ ውሳኔዎች እንደሚያስተላልፍ እምነታቸው እንደሆነም ተናግረዋል። በየአከባቢው የሚታዩ ግጭቶች ፣ብሄር ተኮር ጥቃትና ለህዝብ የማይጠቅም ጽንፈኛ አስተሳሰብ በማስወገድ ኢህአዴግ ወደ ቀድመው አንድነቱ የሚያመጡትን ውሳኔዎች ያሳልፋል ያሉት ደግሞ የሰቲት ሁመራ ነዋሪው አቶ አስረስ ደበበ ናቸው። እየተካሔደ ባለው ድርጅታዊ ጉባኤ በየጊዜው እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚረዱ ጠቃሚ ውሳኔዎች ይተላለፋሉ ብለው እንደሚጠብቁ ጠቁመዋል። "አገራዊ አንድነት ለሁለንተናዊ ብልጽግና" በሚለ መሪ ቃል ዛሬ የተጀመረው የኢህአዴግ 11ኛው ድርጅታዊ ከአጋር ድርጅቶች ተወካዮች፣ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ተጋባዥ የውጭ ሀገራት የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች እና ሌሎች በመሳተፍ ላይ ናቸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም