ቀጥታ፡

የኮንሶ መልክዓ ምድር ይዘትና ደህንነት ጉዳት እየደረሰበት ነው - ምሁራን

ዲላ ጥር 08/2015 (ኢዜአ) በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የኮንሶ መልክዓ ምድር ይዘትና ደህንነት ለተለያዩ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች መጋለጡን የዘርፉ ምሁራን ተናገሩ።

በክልሉ የሚገኙ ቅርሶች ደህንነትና ጥበቃን ለማጠናከር የሚያስችሉ መመሪያዎችና ደንቦች ተረቀው ሊተገበሩ መሆኑን የደቡብ ክልል አስታውቋል።

የዲላ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር አብዮት ለገሰ የኮንሶ መልክዓ ምድር ለተለያዩ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች መጋለጡን ጠቅሰዋል።

ቅርሱ በስርዓተ ትምህርት ትኩረት ያልተሰጠው መሆኑ፣ በህዝብ ቁጥር መጨመር፣ በከተማ መስፋፋት፣ በዙሪያው ጥንቃቄ ያልተደረገበት የልማት ፕሮጀክቶች ንድፍና ትግበራ እና ሌሎች ምክንያቶች ለአደጋው መንስኤ መሆናቸውንም አስረድተዋል።

የቅርሱን ይዘትና ደህንነት መጠበቅ ካልተቻለም ሃብቱን ከማጣት ባለፈ ከዓለም ቅርስነቱ የመሰረዝ አደጋ እንደተጋረጠበት ገልጸዋል።

ለዚህም በምርምር የታገዘ ሳይንሳዊ መፍትሄ በማበጀት ከመንግስት፣ ከአካባቢው ህዝብና ከሌሎች ባለድርሻዎች ጋር በቅንጅት በመተግበር ቅርሱ ደህንነቱ እንዲጠበቅ መስራት እንደሚገባ አመላክተዋል።

ለቅርሶች ጥበቃ በዋናነት ባህላዊ የእውቀት ሽግግር ከትውልድ ወደ ትውልድ ማስተላለፍ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ የጠቀሱት ደግሞ የዓለም አቀፉ የሳይንስ አካዳሚ አባል ዶክተር ዮናስ በየነ ናቸው።

የኮንሶ መልክዓ ምድር ማህበረሰቡ ከ500 ዓመታት በፊት ጀምሮ ጠብቆ ያቆየው ሀብት ሆኖ በዓለም ማህበረሰብ እውቅና እንዲያገኝ ያደረጉት ቱባ ዕሴቶች ያለው መሆኑን ተናግረዋል።

ይሁንና ቅርሱ ባሁኑ ወቅት የተጋረጡበትን ተጽእኖዎች ተቋቁሞ ለማስቀጠል የምሁራን፣ የማህበረሰቡንና የመንግስትን ትኩረት የሚፈልግ መሆኑን አስረድተዋል።

ሌላኛው የቅርስ ተመራማሪ ዶክተር መታሰቢያ በቀለ በበኩላቸው የኮንሶ መልክዓ ምድር የተለያዩ አደጋዎች እንደተጋረጡበት ጠቅሰው ችግሩን ለመቅረፍ አፋጣኝ ምላሽ እንደሚያስፈልገው ጠቅሰዋል።

የኮንሶ መልክዓ ምድር ተጠብቆ እንዲቆይ ለተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሲተገበሩ የኖሩና በብሔሩ የሚታወቁ ማህበራዊ ተቋማቱን ማጠናከር እንደሚገባም መክረዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የደቡብ ክልል የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አበባየሁ ታደሰ በጉዳዮ በሰጡት ምላሽ የክልሉ መንግስት ለቅርስ ጥበቃ ተገቢው ትኩረት እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።

ለዚሁም በክልሉ ለቅርስ ጥበቃ የጸደቀው አዋጅ ማስተግበሪያ ደንብ፣ መመሪያና ፖሊሲ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ ስራዎች መጀመራቸውን አስረድተዋል።

ይህም የኮንሶን መልክዓ ምድር ጨምሮ ሌሎች በክልሉ የሚገኙ አለም አቀፍ ቅርሶች ተገቢው ትኩረትና ጥበቃ እንዲያገኙ ከማድረግ ባለፈ የህግ ተጠያቂነትን እንደሚያስፍንም አብራርተዋል።

በኮንሶና አካባቢው በተለያዩ ምክንያቶች ተከስቶ የነበረው የሰላም መደፍረስ በቱሪዝም ፍሰቱና በቅርሱ እንክብካቤና ጥበቃ ላይ ጫና ማሳደሩን የሚናገሩት ደግሞ የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ኤልያስ ሽኩር ናቸው።

ቅርሱ የተጋረጠበት አደጋ ዘርፈ ብዙ በመሆኑ በምርምርና ጥናት ሳይንሳዊ መፍትሄ ለመስጠት ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተለይ አሁን ያለውን ሰላም በመጠቀም ህብረተሰቡን በነቂስ ያሳተፈ የመልክዓ ምድሩን ይዘትና ደህንነት ጥበቃ ለማድረግ ጥረት እንደሚደረግ ገልጸዋል።

ዲላ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ የሶስት ሀገራት ዩኒቨርሲቲዎች የሚሳተፉበት የኮንሶ መልክዓ ምድር  ጥበቃ ላይ ያተኮረ የምርምር ፕሮጀክት በዲላ ከተማ ይፋ መደረጉን መዘገባችን ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም