ኪነ-ጥበብ በህዝቦች መካከል ጠንካራ ትስስርና መስተጋብር እንዲኖር ጉልህ ሚና አለው--የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ኪነ-ጥበብ በህዝቦች መካከል ጠንካራ ትስስርና መስተጋብር እንዲኖር ጉልህ ሚና አለው--የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር

አዳማ (ኢዜአ) ጥር 08/2015 ኪነ-ጥበብ በህዝቦች መካከል ጠንካራ ትስስርና መስተጋብር እንዲኖር ጉልህ ሚና እንዳለው በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የኪነ ጥበብና ስነ ጥበብ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ነፊሳ አልማህዲ ገለጹ።
ኪነ-ጥበብ በህዝቦች መካከል ጠንካራ ትስስርና መስተጋብር ለመፍጠር ያለውን ሚና ለማጎልበት የዘርፉ ሙያተኞችና ማህበራት የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ ተጠይቋል።
የኪነ-ጥበብ እና ስነ-ጥበብ ሙያተኞችና የዘርፉ የሙያ ማህበራት የተሳተፉበትና ለሁለት ቀናት የሚቆየው የምክክር መድረክ በአዳማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የኪነ-ጥበብ እና ስነ-ጥበብ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ነፊሳ አልማህዲ በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት ኪነ ጥበብ በህዝቦች መካከል ጠንካራ ትስስርና መስተጋብር እንዲፈጠር የጎላ ሚና አለው።
በተለይም የህዝቦችን የአብሮነት እሴቶችን በማጎልበትና በማበልጸግ የሰላምና እርቅ ባህል ለማዳበር ወሳኝነት ያለው ዘርፍ መሆኑን ገልጸዋል።
ዘርፉ በማህበረሰቡ ውስጥ ያሉትን ተጨባጭ ባህላዊ እሴቶች እንዲሁም ወግና ልማዱን በማንፀባረቅ ረገድ የሚጠበቅበትን እንዲያበረክት የዘርፉ ሙያተኞችና ማህበራት በተገቢው መንቀሳቀስ አለባቸው ብለዋል።
ፈጠራን ለማበረታታትና የስራ አማራጮችን ለማስፋትም ኪነ-ጥበብ በሀገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ውስጥ የሚገባውን ድርሻ እንዲያበረክት የሙያው ባለቤቶች ሚና የላቀ መሆኑን አመልክተዋል።
ኪነ-ጥበብ አሉታዊ ትርክቶችን በማረምና በማስተካከል በኩል ድርሻው የጎላ በመሆኑ ዘርፉ ያለውን እምቅ አቅም ለሃገር ግንባታ ለማዋል የተቀናጀ ርብርብ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
በዚህም በሀገር ግንባታ ሂደት ዘርፉ ትልቅ አስታዋጽኦ እንዲያበረክት የኪነ-ጥበብ ሙያተኞችና የዘርፉ የሙያ ማህበራት ሀገራዊ ሃላፊነት መወጣት እንደሚገባቸው ሚኒስትር ዴኤታዋ አስገንዝበዋል።
በሌላ በኩል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ዘርፉ ለሁለንተናዊ ሀገራዊ ብልጽግና አጋዥ እንዲሆን ከማስቻል አንፃር ሰፊ ተግባራት ቢከናወኑም አሁንም ውስንነቶች መኖራቸውን ወይዘሮ ነፊሳ ገልጸዋል።
በተለይም የኪነ-ጥበብ መሰረት ልማት፣ የዘርፉ የኢንቨስትመንት ማበረታቻ፣ የአደረጃጀትና ህግ ማዕቀፎች ክፍተት፣ የፋይናንስና ብድር አገልግሎት ችግር አሁንም በዘርፉ የሚታዩ ማነቆዎች መሆናቸውን አንስተዋል።
ማነቆዎቹን በመፍታት ዘርፉ በሀገራዊ ልማትና ዕድገት የራሱን ሚና መጫወት እንዲችልም ሚኒስቴሩ በባህል እንዲሁም በዕደ-ጥበብ እና ኪነ-ጥበብ ዘርፍ በርካታ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማህበራዊ ልማት ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ዶክተር ኬይረዲን ተዘራ በበኩላቸው ኪነ-ጥበብ በሀገር ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስኮች ውስጥ ወሳኝ ሚና መጫወት የሚችል ዘርፍ ነው ብለዋል።
በተለይም ኢትዮጵያ ከጥንተ ስልጣኔዋ አንስቶ በዓለም ፊት አይበገሬ ሆና የዘለቀችው በኪነጥበቡ ዘርፍ ባላት ሀብት መሆኑን በማውሳት ነገር ግን ዘርፉ ባለው አቅም ልክ አገሪቱ ጥቅም አለማግኘቷንም አንስተዋል።
መድረኩ በዘርፉ ያለውን ችግር በአግባቡ ለመረዳት የሚያስችል ከመሆኑም ባለፈ ምክር ቤቱ ለሚያደርገው ክትትልና ቁጥጥር ስራም ግብዓትና አመችነትን የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።
ለሁለት ቀናት በተሰናዳው ምክክር የኪነ-ጥበብ እና ስነ-ጥበብ የፈጠራ ዘርፉ ለእድገቱና ማህበራዊ መስተጋብሩ ተገቢውን ሚና እንዲወጣ የዘርፉ ሙያቶችና ባለድርሻ አካላት ምን ሰርተዋል? ምንስ አልሰሩም? በሚለው ተገቢውን ግምገማ አድርገው ቀጣይ አቅጣጫ እንደሚያስቀምጡ ይጠበቃል።