በአማራ ክልል የሚገኙ የባህል እሴቶችን በማስተዋወቅና በማሳደግ ለቱሪዝም ለማዋል ይሰራል-- ዶክተር ጌታቸው ጀምበር - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል የሚገኙ የባህል እሴቶችን በማስተዋወቅና በማሳደግ ለቱሪዝም ለማዋል ይሰራል-- ዶክተር ጌታቸው ጀምበር
ጎንደር (ኢዜአ) ጥር 8/2015 በአማራ ክልል የሚገኙ የባህል እሴቶችን በማስተዋወቅና በማሳደግ ለቱሪዝም ለማዋል እንደሚሰራ የክልሉ ምክትል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ጌታቸው ጀምበር ተናገሩ፡፡
በክልሉ ቱሪዝምን ለማሳደግ ያለመ 'የወይዘሪት ቱሪዝም አማራ' ቁንጅና ውድድር እውቅና እና የሽልማት መርሀ-ግብር በጎንደር አጼ ፋሲል ቤተ-መንግስት ተከናውኗል፡፡
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት የቱሪዝም ዘርፉ በክልሉ ሰፊ የስራ እድል መፍጠሪያና የኢኮኖሚ አቅም ነው።
''በክልሉ በስፋት ያላስተዋወቅናቸውና ያላለማናቸው የብዝሃ ባህል እሴት የሆኑ ባህላዊ አለባበስ፣ አመጋጋብና አኗኗርን የመሳሰሉ ቱባ ባህሎች አሉ'' ብለዋል።
እነዚህ የባህል እሴቶች የሀብት ምንጭ ሆነው ሊያገለግሉ የሚችሉና የክልሉን ኢኮኖሚ እንዲደግፉ በትኩረት እንደሚሰራባቸው ገልጸዋል፡፡
በክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የተጀመረው የባህል እሴቶችን ለቱሪዝም የማዋል በጎ ጅምር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቅሰው፤ የቁንጅና ውድድሩም የክልሉን የቱሪዝም ሀብት ከማስተዋወቅ አንጻር ፋይዳው የጎላ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በአማራ ክልል ካለው እምቅ የባህል ሀብት አንጻር ዘርፉን በማሳደግ፣ በማልማትና በማስተዋወቅ ረገድ ብዙ መስራት ይጠይቃል ያሉት ደግሞ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ አቶ ጣሂር መሀመድ ናቸው፡፡
የባህል ጸጋዎችን መነሻ በማድረግ የዘርፉን አቅም ይበልጥ ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት በማከናወን የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡'
የወይዘሪት ቱሪዝም አማራ ቁንጅና ውድድር' የእውቅና እና ሽልማት መርሃ-ግብር የክልሉን ባህልና ታሪክ ከማስተዋወቅ አንጻር በጎ ጅምር በመሆኑ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል፡፡
የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዘውዱ ማለደ በበኩላቸው የቁንጅና ውድድሩ በከተማው መካሄዱ ለጥምቀት በአል ድምቀት ልዩ ድባብ ከመፍጠሩም በላይ ቱሪዝሙን በማነቃቃት የጎላ ፋይዳ አለው ብለዋል፡፡
በእለቱ በተከናወነው የቁንጅና ውድድር አሸናፊ የሆነችው ወይዘሪት ቤዛ ሳህሌ የ100 ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶላታል፡፡
ወይዘሪት ሄለን መኳንንት ሁለተኛ እንዲሁም ወይዘሪት ትእግስት ባንተይገኝ ደግሞ ሶስተኛ ደረጃን በማገኘት ውድድራቸውን አጠናቀዋል፡፡
በመዝጊያ ስነ-ስርአቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኘቸው የክብር ዶክተር አርቲስት ማሪቱ ለገሰ ልዩ ተሸላሚ ሆናለች፡፡
በመርሀ ግብሩ ላይ የክልልና የዞን ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎችን ጨምሮ ታዋቂ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡