አፍሪካ በዓለም አትሌቲክስ የአመራር ሥርዓት ውስጥ ተገቢውን ውክልና እንድታገኝ በጋራ መሠራት አለበት - አፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌደሬሽን

266

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 7 ቀን 2015 አፍሪካ በዓለም አትሌቲክስ የአመራር ሥርዓት ውስጥ ተገቢውን ውክልና እንድታገኝ በትብብር መሥራት እንደሚገባ የአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ሀማድ ካልካባ ጥሪ አቀረቡ።

ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ አትሌቲክስ ሪጅን ጉባኤ በኢትዮጵያ ስካይላይት ሆቴል ተካሂዷል። 

የአፍሪካ አትሌቲክ ኮንፈደሬሽን ፕሬዝዳንት ሀማድ ካልካባ ምስራቅ አፍሪካ የሯጮች ምድር መሆኑን አስታወሰው ይህም ለቀጠናው ብቻ ሳይሆን መላው አፍሪካዊን ኩራት ነው ብለዋል።

 ይህን በአትሌቲከስ ስፖርት ያለውን ውጤታማነት የሚያስጠብቅና ቀጣይነት እንዲኖረው የተለያዩ ተግባራትን በትብብር መሥራት እንደሚገባም ነው ያነሱት። 

አፍሪካዊያን ከአትሌቲክስ ልማት ጎን ለጎን በዓለም አቀፍ የዓለም አትሌቲክስ አመራር ሥርዓት ዘንድ አፍሪካ ያላትን ውክልና ለማሳደግ በጋር መስራት እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል። 

ይህም በአትሌቲክስ ጉዳዮች በሚወሰኑ ጉዳዮች ያላትን ተሳትፎ በማሳግ የአፍሪካ አትሌቲከስ ጥቅምና መብት ለማስከበርም የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው አንስተዋል። 

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንትና የምስራቅ አፍሪካ አትሌቲክስ ሪጅን ምክትል ፕሬዝዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ ወጣቶችን ለማፍራት የሥልጠና ማዕከላትን ግንባታ ላይ በትብብር ስለሚሰሩበቻው ጉዳዮች መወያየታቸውን ገልፃለች።

 በተለይ በቀጣይ አራት ዓመት ውስጥ አበራታች ቅመሞችን መከላከል ላይ ሰፊ ትኩረት ተሰጥቶ ለመሥራት የሚያስችሉ ውይይቶች መደረጋቸውን ጠቅሳለች። 

የምስራቅ አፍሪካ አትሌቲክስ ሪጅን ኮንግረስና የኬኒያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ጀነራል ጃክሰን ትዊ በዛሬው ጉባኤ የአትሌቲከስ ልማትን ለማሳደግ በምን መልኩ መሥራት እንደሚገባ ውይይት መደረጉን ገልጸዋል። 

ከዚህ በተጨማሪ የአበረታች ቅመሞች ጉዳይም ሰፊ ውይይት እንደተደረገበት ነው ያነሱት። 

በዛሬው በተደረገው ጉባኤ የምስራቅ አፍሪካ አትሌቲክስ ሪጅን ኮንግረስ ለቀጣይ አራት አመታት ሪጅኑን የሚመሩ የፕሬዝዳንትና የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላትን መርጧል። 

በዚህ መሰረትም የምስራቅ አፍሪካ አትሌቲክስ ሪጅን ኮንግረስ እንዲመሩ ጀነራል ጃክሰን ቲዊ በፕሬዚዳንትነት ተመርጠዋል። 

እንዲሁም ዶሚኒክ ኡትሲት ከኡጋንዳ ተቀዳሚ ምክል ፕሬዝዳንትና፣ ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ ከኢትዮጵያ ምክትል ፕሬዝዳንት አድረጎ መርጧል። 

በጉባኤው በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት ጨምሮ ሌሎች የጉባኤው አባላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም