የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች ለመፍታት እየተሰራ ነው-ዶክተር ደረጀ ዱጉማ

አርባ ምንጭ (ኢዜአ) ጥር 07/2015 (ኢዜአ) የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች በተቀናጀ መንገድ ለመፍታት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ ገለጹ፡፡

የደቡብ ክልል 10ኛው የማህረሰብ አቀፍ ጤና መድህን የተጀመረበትንና የ2015 ክልል አቀፍ ንቅናቄ መድረክ በአርባ ምንጭ ከተማ ተካሂዷል፡፡

በመድረኩ ላይ የተገኙት ዶክተር ደረጀ፤ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ፕሮግራም በየትኛውም ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎች ተገቢና ፍትሃዊ የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ ጉልህ ድርሻ ያለው መርሃ-ግብር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የሀገራችን ብልጽግና ማረጋገጥ የሚቻለው አምራችና ጤናማ ዜጎችን ማፍራት ሲቻል ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሮችን በተቀናጀ መንገድ ለመፍታት ሚኒስቴሩ በትኩረት እየሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡

በተለይ ከመድሃኒት አቅርቦት፣ የሙያ ስነ-ምግባርና ብልሹ አሠራር ጋር ከአባላቱ በተደጋጋሚ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ጥራት ያለውና ፍትሃዊ የጤና አገልግሎት ለህብረተሰቡ መስጠት እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

በሀገር ደረጃ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ፕሮግራም ማሳካት የሀገራችን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ ትልቅ ድርሻ ያለው በመሆኑ በየደረጃው የሚገኙ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች የበኩላቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል፡፡

የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍሬህይወት አበበ፤ በሀገሪቱ ባለፉት 10 ዓመታት በተከናወኑ ተግባራት የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ተደራሽነት ከ90 በመቶ በላይ መድረሱን ገልጸዋል፡፡

ሆኖም ፍትሃዊና ጥራት ያለው አገልግሎት ከመስጠት አንጻር ያሉትን ውስንነቶች ማስተካከል ተቀዳሚ ስራችን ነው ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ፕሮግራምን በማሳካት ጤናማና አምራች ትውልድ ለማፍራት በሚደረገው ጥረት በየደረጃው የሚገኙ የዘርፉ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት በተደረገው ርብርብ ከ7 ሚሊዮን በላይ የክልሉ ነዋሪዎች የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የገለጹት ደግሞ የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ ሃላፊ አቶ እንዳሻው ሽብሩ ናቸው፡፡

ይሁን እንጂ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በዘርፉ ላይ የሚነሱ ቅሬታዎችን በዘላቂነት ለመፍታት እንዲቻል ከጤና ተቋማትና ሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

ተደራሽነትን ለማስፋት በሚሰጠው ትኩረት ልክ የተሳለጠና ፍትሃዊ አገልግሎት ለማዳረስም ከግንዛቤ ማጎልበት ጀምሮ አቅርቦት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ አቶ እንዳሻው ገልጸዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ ባለፉት 10 ዓመታት በክልሉ በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት የተከናወኑ ተግባራት አጠቃላይ ጠንካራና ደካማ ጎኖችን የሚያሳይ ሪፖርት ቀርቦ ውይይት የተደረገበት ሲሆን የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ መዋቅሮች የማበረታቻ የምስክር ወረቀትና ዋንጫ ተበርክቶላቸዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳውን ጨምሮ ሌሎችም የፌዴራልና ክልል ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም