በደቡብ ወሎ እና በምስራቅ ጎጃም ዞኖች በ56 ሺህ 780 ሄክታር መሬት ላይ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ሥራ ለማከናወን ዝግጅት መደረጉ ተገለጸ

ደሴ/ደብረ ማርቆስ (ኢዜአ) ጥር 7/2015 በደቡብ ወሎ እና በምስራቅ ጎጃም ዞኖች በ56 ሺህ 780 ሄክታር መሬት ላይ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ሥራ ለማከናወን ዝግጅት መጠናቀቁን የዞኖቹ ግብርና መምሪያዎች አስታወቁ።

በዞኖቹ የ2015 ዓ.ም የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ የንቅናቄ መድረክ በደሴ ከተማና በአዋበል ወረዳ ተካሂዷል።

የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አህመድ ጋሎ እንደገለጹት፣ በዘንድሮው የበጋ ወራት 1 ሺህ 398 የተመረጡ ተፋሰሶች ላይ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ ይከናወናል።

በዚህም ከ35 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት ላይ አፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ለማከናወን ከመሳሪያ ዝግጅት ባለፈ ቀያሽ አርሶ አደሮችና ባለሙያዎች ተለይተው ስልጠና መሰጠቱን ጠቁመዋል።

ከተያዘው ጥር ወር አጋማሽ ጀምሮ ለተከታታይ 30 ቀናት በሚከናወነው ልማት ከ600 ሺህ ህዝብ በላይ ለማሳተፍ በየደረጃው የንቅናቄ ሥራ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱ ሁሴን በበኩላቸው፣ የዘንድሮውን የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ስራ ውጤታማ ለማድረግ ካለፉት ዓመታት ልምዶች መወሰዳቸውን ጠቁመዋል።

"አመራሩና ህብረተሰቡ ተቀናጅተው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ከማከናወን ባለፈ ያለሙ አካባቢዎች በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲለሙ አቅጣጫ ተቀምጧል፤ ከወዲሁ ቅድመ ዝግጅትም ተደርጓል" ብለዋል።

በተመሳሳይ በምስራቅ ጎጃም ዞን በበጋው ወራት የሚሰራውን የአፈርና የውሃ ጥበቃ ሥራ በተቀናጀ መንገድ ለማከናወን በአዋበል ወረዳ የንቅናቄ መድረክ ተካሄዷል። 

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም አያሌው በዚህ ወቅት እንዳሉት በዞኑ ባለፉት ዓመታት በአፈር እና ውሃ ጥበቃ ስራዎች ውጤት ተመዝግቧል። 

ይህንን የበለጠ በማጠናከር ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት በትኩረት መስራት እንደሚገባም አመልክተዋል። 

"ለዚህ ደግሞ የልማት ሥራው ለተወሰኑ አካላትና ለአርሶ አደሩ ብቻ የሚተው ሳይሆን ባለሀብቱ፣ የከተማው ማህበረሰብ እና ተማሪው በንቅናቄው መሳተፍ ይገባቸዋል" ሲሉ አስገንዝበዋል። 

ባላፉት ዓመታት የተከናወኑ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራዎች ለሰብል ምርታማነት መጨመር፣ ለመስኖ ልማት፣ ለንብ ማነብና ለእንስሳት ማድለብ አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የዞኑ ግብርና መምሪያ ሃላፊ አቶ ፈንታሁን ቸኮል ናቸው። 

በበጀት ዓመቱ በዞኑ ከ1ሺህ 80 በሚበልጡ ተፋሰሶች በ21ሺህ 781 ሄክታር መሬት ላይ የአፈር እና ውሃ ጥበቃ ሥራ እንደሚከናወን ገልጸዋል። 

የልማት ሥራው ከጥር 15 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ለ21 ተከታታይ ቀናት እንደሚከናወን ጠቁመዋል።  

በልማት ሥራው በየቀኑ ከ619 ሺህ በላይ ሰዎች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁመው፣ "በዚህም የማሳ ላይ እርከን፣ ቦረቦር ማዳንና መሰል የልማት ሥራዎች ይከናወናሉ" ብለዋል። 

በንቅናቄ መድረኩ ከዞን እስከ ወረዳ ያሉ የግብርና ባለሙያዎች፣ አመራሮች እንዲሁም የፍትህና የፀጥታ አካላት ተሳትፈዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም