ቀጥታ፡

ኢህአዴግ እንደስያሜው የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ድርጅት ይሆናል-ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ

አዲስ አበባ መስከረም 23/2011 የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር እንደስያሜው የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ድርጅት ይሆናል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሀዋሳ በመካሄድ ላይ ያለውን 11ኛው የኢህአዴግ ጉባኤ ሲከፍቱ እንዳሉት አጋር ድርጅቶችን ኢህአዴግ ውስጥ ማካተት ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ሲታሰብበት ቆይቷል። በዚሁ ላይ ጥናት መደረጉንም ገልጸው ባለፉት አመታት በነበረው አገራዊ ሁኔታ ምክንያት ውህደቱ ለዘንድሮው ጉባኤ ሊደርስ አለመቻሉን ግን ጠቁመዋል። ይሁንና ጉባኤው ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር  የሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጎች ድርጅት መሆን እንዲችልና ሁሉም አመራር የሚሆንበትን ሁኔታ ለመፍጠር የተለየ አቅጣጫ ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል ነው ያሉት። ይህ እውን እንዲሆን በመስራትም ኢህአዴግን እንደስያሜው የኢትዮጵያዊያን ፓርቲ ማድረግ የሁሉም ኃላፊነት መሆኑን አመልክተዋል። እስከ መስከረም 25 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ የሚካሄደው የኢህአዴግ 11ኛው ድርጅታዊ ጉባዔ በ10ኛው ጉባዔ ላይ የተቀመጡ አቅጣጫዎች እና የተላለፉ ውሳኔዎች አፈፃፀመን የሚገመግም ይሆናል። በተጨማሪም ባለፉት አምስት ወራት በአመራሩ ሲወሰዱ የነበሩትን ለውጦች አጠናክሮ ማስቀጠል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይም ይመክራል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም